ፍቺ / ካርሎስ ቴቬዝ ከቻይናው ሻንጋይ ሼንዋ ጋር የነበረው ቆይታ ከአንድ አመት በኋላ ተቋጨ

አርጀንቲናዊው ካርሎስ ቴቬዝ በቻይና ያደረገው ያልተሳካ ቆይታ በኋላ ከክለቡ ሻንጋይ ሼንዋ ጋር ተነጋግሮ ውሉ ሊጠናቀቅ አንድ አመት እየቀረው በጋራ ስምምነት ኮንትራቱን ቀደደ።

ሻንጋይ ሼንዋ ዛሬ ይፋ ባደረገው መሰረት ከአሁን በኋላ ከአርጀንቲናዊው የቀድሞ የማንችስተር ዩናይትድ እና ማን ሲቲ አጥቂ ከነበረው ካርሎስ ቴቬዝ ጋር ተለያይቷል።

“ክለቡ ባለፈው አመት ቴቬዝ ላበረከተው አስተዋፅኦ እያመሰገነ ለወደፊቱም መልካም ነገር እንዲገጥመው ይመኛል።” በማለት መለያየታቸውም ይፋ አድርገዋል።

33ኛ አመቱ ላይ የሚገኘው ቴቬዝ በታህሳስ 2016 ሻንጋይ ሼንዋን ከተቀላቀለ በኋላ በ 20 ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎ 4 ጎሎችን ብቻ ማስቆጠር ችሏል።

የፕሮፌሽናል የእግርኳስ ህይወቱን ከቦካጁኒየርስ ጋር የጀመረው ቴቬዝ በ 2005/2006 ከብራዚሉ ኮረንቲያስ ጋር ቆይታ ካደረገ በኋላ ከሌላው የቡድን አጋሩ ማቼራኖ ጋር በመሆን ወደ ዌስትሀም ማቅናታቸው ይታወሳል።

በዌስትሀም መልካም አጀማመር ያደረገው ቴቬዝን ማን ዩናይትዶች ካስፈረሙት በኋላ በክለቡ ሁለት አመት ቆይታ አድርጎ 19 ጎሎችን ከመረብ ጋር ማገናኘት ችሏል።

በመቀጠል በአወዛጋቢ ሁኔታ ማን ሲቲዎን በመቀላቀል በሁለት  አመት ውስጥ 43 ጎሎችን በማስቆጠር 2012 ላይ ሲቲዎች የፕሪምየርሊጉን ዋንጫ እንዲያነሱ አግዟል።

በሴሪኣውም በጁቬንቱስ ቆይታ ካደረገ በኋላ ወደ ሀገሩ ተመልሶ ከቦካጁኒየርስ ጋር በመሆን የእግርኳስ ህይወቱን እንደሚያጠናቅቅ ቢጠበቅም ሳይታሰብ በ 615 ሺ ፓውንድ ሳምንታዊ ደሞዝ ወደ ቻይና አቅንቶ ላለፉት አንድ አመት ሲጫወት ቆይቷል።

ነገርግን በቻይና የነበረው ጊዜ በአቋም መውረድ እና ሰውነቱ በመወፈሩ ከክለቡ አሰልጣኝ ጭምር ለትችት ተጋልጦ እንደነበረ የሚታወስ ሲሆን መጨረሻውም ከክለቡ ጋር መለያየቱ እርግጥ ሆኗል።

ቴቬዝ በድጋሚ ወደ ሀገሩ በመመለስ ከቦካ ጁኒየርስ ጋር ልምምድ መስራት መጀመሩን ክለቡ የተጫዋቹን ምስል በድረገፁ በመልቀቅ አሳውቋል።

ቦካጁኒየርስ በአርጀንቲና የመጀመሪያ ዲቪዚዮን ከ 12 ጨዋታዎች 30 ነጥብ በመሰብሰብ ሁለተኛ ላይ ከተቀመጠው ሳን ሎሬንዞ በሶስት ነጥቦች ከፍ ብሎ ተቀምጧል።

Advertisements