ሊቨርፑል በ 2017/2018 የውድድር አመት የኮቲንሆን ማሊያ ገዝተው ለነበሩ ደጋፊዎቹ ማካካሻ አዘጋጀ

ብራዚላዊው ፍሊፔ ኮቲንሆ ወደ ባርሴሎና ማቅናቱን ተከትሎ ሊቨርፑል ለ2017/2018 የውድድር አመት የተጫዋቹን ማሊያ ገዝተው ለነበሩ ደጋፊዎች ላወጡት ወጪ ማካካሻ አዘጋጀ።

ትናንትና[ቅዳሜ] ምሽት ሁለቱ ክለቦች በኮቲንሆ ዝውውር ዙሪያ ላይ መስማማታቸው ከታወቀ በኋላ ሊቨርፑል ተጫዋቹ የህክምና ምርመራውን ካጠቀቀ በኋላ ክለቡን እንደሚለቅ አሳውቋል።

ባርሴሎናም በበኩሉ የተጫዋቹ ዝውውርን “እንኳን ደህና መጣህ” በማለት ዝውውሩን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ተጫዋቹ በክረምቱ ዝውውሩን ማጠናቀቅ ባለመቻሉ እስከ ጥር ድረስ በሊቨርፑል መቆየት ችሏል።የተጫዋቹ መቆየት ተከትሎ ደጋፊዎች በውድድር አመቱ መጀመሪያ ላይ 10 ቁጥር ያረፈበት የተጫዋቹ ማሊያ ሲገዙ ቆይተዋል።

ነገርግን ዝውውሩ አሁን በመጠናቀቁ ደጋፊዎች በብስጭት የተጫዋቹን ማሊያ ማቃጠል ቢጀምሩም ክለቡ ግን የኮቲንሆን ማሊያ ገዝተው ለነበሩ ደጋፊዎች ላወጡት ወጪ ማካከሻ ፈጥሮላቸዋል።

ይህንን ለመተካት ክለቡ ደጋፊዎች ከይፋዊ የክለቡ ሱቅ ወይንም በክለቡ ድረገፅ ማሊያውን የገዙበትን ደረሰኝ ይዘው በማንኛውም የክለቡ ይፋዊ ሱቅ በመቅረብ ያወጡት ወጪ 50 ፓውንድ ተመላሽ እንደሚደረግላቸው ታውቋል።ነገርግን ደጋፊዎቹ ማሊያውን ተመላሽ አያደርጉም።

ደረሰኙ ከጥር 13 እስከ ግንቦት 31/2018 ድረስ ላቀረቡ ወጪው የሚመለስላቸው ሲሆን ደጋፊዎቹ ግን መቅረብ ያለባቸው በእንግሊዝ እና በአየርላንድ ያሉ የክለቡ ሱቆች ብቻ እንደሆነ ነው የተገለፀው።

Advertisements