ሽኝት / ስቶክ ሲቲ ማርክ ሂውዝን አሰናበተ

ስቶክ ሲቲ በኤፍኤ ዋንጫ ጨዋታ ሶስተኛ ዙር በኮቨንተሪ ሲቲ ሽንፈት ከደረሰበት በኋላ አሰልጣኝ ማርክ ሂውዝን አሰናብቷል። 

በምሽቱ ግጥሚያ በታችኛው የሁለተኛ ሊግ ተሳታፊው ኮቨንተሪ የ 2-1 አስደንጋጭ ሽንፈት የገጠመው ስቶክ በቋፍ ላይ የነበሩትን አሰልጣኙን ጨዋታው ከተጀመረበት ጥቂት ቆይታ በኋላ ማሰናበቱን በይፋ አስታውቋል።

ስቶክ በይፋዊ የትዊተር ገፁ ባሰፈረው መግለጫም “ስቶክ ሲቲ ከአሰልጣኝ ማርክ ሂውዝ ጋር የነበረውን ውል አፋጣኝ ተፅዕኖ ባለው መልኩ አቋርጦታል።” ሲል አስታውቆ ሂውዝ በክለቡ ለነበራቸው የአራት አመታት ከግማሽ ቆይታ ያለውን ክብር ገልጿል።

በ 2013 ስቶክን የተቀላቀሉት ሂውዝ ከዚህ ቀደም ማንችስተር ሲቲ፣ ፉልሀም እና ኪውንስ ፓርክ ሬንጀርስን ማሰልጠን ሲችሉ በዌልስ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነትም አምስት አመታትን አሳልፈዋል።

ሂውዝ ስቶክን ከያዙ አንስቶ ለተከታታይ ሶስት አመታት የሰንጠረዡ ወገብ ላይ በሆነ ተመሳሳይ የዘጠነኛ ደረጃ ክለቡን በማስጨረስ ስኬታማ ጊዜን ቢያሳልፉም አምና በ 13ኛ ደረጃ ሊጉን መፈፀማቸው የአሰልጣኝነት ወንበራቸውን ማነቃነቅ መጀመሩ አይረሳም።

በዘንድሮው የውድድር ዘመን ደግሞ የክለቡ ውጤት ይበልጥ እያሽቆለቆ መጥቶ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ 18ኛ ደረጃ ላይ ሆኖ የመጀመሪያ ዙሩን ማጠናቀቁ ስንብታቸውን አይቀሬ አድርጎታል።

ስቶክ በዘንድሮው የ 2017/18 የውድድር ዘመን ካደረገው 22 ጨዋታ ድል ማድረግ የቻለው በአምስቱ ብቻ ነው።

Advertisements