ተሞክሮ / የኪክ ቦክስ የአሰልጣኞች ስልጠና ተካሄደ

በሀገራችን ለሚገኙ የማርሻል አርት አሰልጣኞች የኪክ ቦክስ የአሰልጣኞች ስልጠና ከፊላንድ በመጡት የቀድሞ ፕሮፌሽናል የኪክ ቦክስ ተፋላሚና የአሁኑ አሰልጣኝ ጃኮ ጁኩላ ተሰጥቶ በስኬት ተጠናቋል።

ይህ ለሁለት ቀናት የቆየው የስልጠና መርሀ ግብር በመጀመሪያ ቀን ውሎው ቦሌ በሚገኘው የጁፒተር ሆቴል የንድፈ ሀሳብ (theory) ቆይታ የተደረገበት ሲሆን በሁለተኛው ቀን ውሎ ደግሞ ካዛንቺስ በሚገኘው የጁፒተር ሆቴል ቅርንጫፍ የተግባር ልምምድ ተስተናግዶበታል።

በመጀመሪያ ቀን ውሎም በፕሮፌሽናል እና አማተር የፍልሚያ መንገድ (fighting style) ዙሪያ ሶስት ንዑስ ጉዳዮችን የያዙ ስልጠናዎች የተሰጡ ሲሆን በዚህም መሰረት በኪክ ቦክስ ተፋላሚዎች አመጋገብ፣ የልምምድ መንገዶችና የልምምድ ሰዓታት ቆይታ እንዲሁም በመነሳሳት (motivation) እና በአሰለጣጠን፣ የተፋላሚዎች የአናናር ዘይቤ ዙሪያ ትኩረት ያደረጉ እያንዳንዳቸው የ 45 ደቂቃዎች ቆይታዎችና አጠቃላይ የሶስት ሰአት የንድፈ ሀሳብ ስልጠና ተካሂዷል።

በሴሚናሩ ላይ ከአሰልጣኝ ጃኮ በተሰጡ ስልጠናዎች ዙሪያ የስልጠናው ተሳታፊዎች ያላቸውን አስተያየትና በስልጠናው ላይ ወይም ከዚህ ቀደም በማሰልጠን ሂደታቸው ያጋጠማቸውን ከኪክ ቦክስ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች አቅርበው ከመድረኩ መልስ ተሰጥቷቸዋል።

ካዛንቺስ በሚገኘው የጁፒተር ሆቴል በተካሄደው የሁለተኛው ቀን የስልጠናው ውሎ ደግሞ አጠቃላይ ለሶስት ሰአታት የቆየ ከ 15 ደቂቃ እስከ 30 ደቂቃ ቆይታ የነበራቸው የተግባር ስልጠና በጃርኮ መሪነት ተካሂዶ ተጠናቋል።

የአለምአቀፍ ኪክ ቦክስ ፍልሚያ አምባሳደር በመሆን በራሳቸው ተነሳሽነት እያገለገሉ ያሉት አሰልጣኝ ጃኮ ከዚህ ቀደም ታንዛኒያና ዛንዚባርን የመሳሰሉ ሀገራት በማምራት ተመሳሳይ ስልጠናዎችን የሰጡ ሲሆን ከሁለት አመታት በፊት ከኪክ ቦክስ ፍልሚያ ራሳቸውን ከማገለላቸው በፊት በ 54 አገራት በመዘዋወር 200 ያህል ፍልሚያዎችን ማድረጋቸውንና ለሶስት ጊዜያት የአለም የኪክ ቦክስ ሻምፒዮና መሆን መቻላቸውን ከስልጠናው በኋላ ኢትዮአዲስ ስፖርት ጋር በነበራቸው ቆይታ አውስተዋል።

ፊንላንዳዊው አሰልጣኝ በስልጠናው ዙሪያ በሰጡት አስተያየትም በስልጠናው ተሳታፊ የነበሩ አካላት ትልቅ ፍላጎትና ተሳትፎ ማድረጋቸውን ገልፀው በቀጣይ የኪክ ቦክስ ስፖርት በኢትዮጵያ እንዲስፋፋም ከሌሎች ሀገራት ፌደሬሽኖች እና ሌሎች ስፖንሰሮች ድጋፍ የሚገኝበትን መንገድ ለማመቻቸት ጥረት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል። 

ጃርኮ በመጨረሻ መልዕክታቸውም የኪክ ቦክስ ስፖርት የኦሎምፒክ ውድድር ድረስ መካተት የቻለ ትልቅ ስፖርት መሆኑን እና መንግስትና የሚመለከታቸው አካላትም ሀገራችን ኢትዮጵያ ከስፖርቱ የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝና በአለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ የሚሆኑ የኪክ ቦክስ ተፋላሚዎችን እንድታፈራ ትልቅ ትኩረትና ድጋፍ እንዲሰጡ አሳስበዋል።

በተመሳሳይ መልኩ ከሰሞኑ ወደቤላሩስ በማምራት በሰባተኛው አለም አቀፍ የማርሻል አርት ውድድር ላይ ተሳትፈው ሜዳሊያ ይዘው የመጡት እና የአዲስ አበባ የተቀናጀ (integrated) ማርሻል አርት የኪክ ቦክሲንግ ቴክኒክ ኮሚቴ የሆኑት ማስተር ኢንስትራክተር አዛዥ አየለ ስልጠናው ጃኮ በአለም አቀፍ ደረጃ የነበራቸውን የውድድር ልምድና የህይወት ተሞክሮ ለሀገራችን አሰልጣኞች እንዲያካፍሉ እገዛ እንዳደረገ ገልፀው ስልጠናው በሀገራችን ኪክ ቦክስን ወደአለም አቀፍ መድረክ ስፖርትነት ለመቀየር ትልቅ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል።

ማስተር አዛዥ በንግግራቸው ስልጠናውን ለማካሄድ አሰልጣኙን ወደሀገራችን ላመጣው ጁፒተር ሆቴል ምስጋና አቅርበው አጋጣሚው ትልቅ እድል መሆኑን እና ሌሎች ባለሀብቶችም የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ቢያደርጉ ስፖርቱ ትልቅ ደረጃ ሊደርስ እንደሚችል ያላቸውን ምልከታ ሰጥተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ማርሻል አርት በዚህ ሰአት በአለም አቀፍ ደረጃ ከኢኮኖሚ እና ፖለቲካዊ አቋም አንፃር ትልቅ ትኩረት እያገኘ ያለ ስፖርት መሆኑን እና በአማተር ደረጃም ጤናን ለመጠበቅና አካላዊ ጥንካሬን ለማግኘት እንደሚረዳ አውስተው የሀገራችን ተወዳዳሪዎች ሰብረው ወደ አለም አቀፍ መድረክ እንዲወጡም ሚዲያን ጨምሮ ባለሀብቶች እንዲሁም ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ማስተር አዛዥ በመጨረሻም የኪክ ቦክስ ስፖርት በሀገራችን መተግበር ከጀመረ ከ 20 አመት በላይ እንዳስቆጠረና ራሱን ችሎ ለመውጣትም ጥረት ላይ መሆኑን ገልፀው በቂ ትኩረት የሚሰጠው ከሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ እንደ አትሌቲክስና እግር ኳስ ትልቅ ስፖርት መሆኑን እና ትልቅ የውጭ ምንዛሪን ለሀገራችን ማምጣት ባለሙያውንም ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል ስፖርት እንደሆነ በመናገር የስፖርቱን ተፅዕኖ አስረድተዋል። 

ኪክ ቦክሲንግ የካራቴና ሙሀይ ታይ ስፖርቶችን በማቀናጀት በሂደት የመጣ እንደሆነ የሚነገርለት የስፖርት አይነት ቢሆንም ዘመናዊ የኪክ ቦክስ ስፖርት ቴክዋንዶ እና የቡጢ (box) ስፖርትን በመቀላቀል እግርና እጅን በጋራ በመጠቀም የሚደረግ ስፖርታዊ ፍልሚያ ነው። 

ኪክ ቦክስ በጃፓን በ 1960ዎቹ መተግበር እንደጀመረ ሲነገር የአሜሪካው ኪክ ቦክሲንግ በበኩሉ በ 1970ዎቹ መተግበር ጀምሮ መስከረም ወር 1974 በተደረገው የመጀመሪያው አለምአቀፍ ሻምፒዮና ምክንያት እውቅና ማግኘት እንደጀመረ በስፖርቱ ዙሪያ የሰፈሩ ታሪካዊ መዛግብት ይጠቁማሉ።

Advertisements