የጆሴ ሞሪንሆ እና የአንቶኒዮ ኮንቴ የቃላት ጦርነት ተጋግሏል።”እሱ ትንሽ ሰው ነው” – አንቶኒዮ ኮንቴ

በፕሪምየርሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ላይ ተከታትለው በተቀመጡት በማን ዩናይትድ እና በቼልሲ አሰልጣኞች በሆኑት ጆሴ ሞሪንሆ እና አንቶኒዮ ኮንቴ መካከል እየተደረገ ያለው የቃላት ጦርነት ተፋፍሞ የተለየ ርእስ ይዞ መነጋገሪያነቱ ቀጥሏል።

ሁለቱ አሰልጣኞች ከ 2016 ጀምሮ አለፍ አለፍ እያሉ እርስበርስ በቃላት ውዝግብ ውስጥ መግባት ከጀመሩ በኋላ ከሰሞኑን ምልልሳቸው ጠንከር እያደረጉት መጥተዋል።

ባለፈው አመት ቼልሲዎች ማን ዩናይትድን 4-0 ሲያሸንፉ አንቶኒዮ ኮንቴ ያሳዩት ስሜታዊ የደስታ አገላለፅ ጆሴ ሞሪንሆን ያስቀየመ ነበር።ጆሴም ይህን አስመልክቶ ኮንቴን መተቸታቸው ይታወሳል።

ለትችቶቹ ምላሽ ከመስጠት ወደኋላ የማይሉት ኮንቴ ሞሪንሆም ድሮ ያሳዩት የነበረው የደስታ አገላለፅን “እራሱ ባለፉት ጊዚያት ያሳለፋቸው የደስታ አገላለፆች ማስታወስ ይኖርበታል።ምናልባትም እያወራ ያለው እሱ ስላሳለፋቸው የደስታ አገላለፅ መሆን አለበት።”በማለት ጆሴ ድሮ የደስታ አገላለፃቸው ስሜታዊነት የታከለበት እንደነበር በማስታወስ የቃላት ጦርነቱን አጋግለውታል።

አርብ በኤፍ ኤ ካፕ ጨዋታ ደርቢ ካውንቲን ካሸነፉ በኋላ በጉዳዩ ላይ ምላሻቸውን የሰጡት ጆሴ በጨዋታ ውጤት በማጭበርበር ቅሌት ምክንያት ተቀጥተው እንደማያቁ፣ወደፊትም እንደማይቀጡ በመናገር አንቶኒዮ ኮንቴን ላይ ትችታቸውን አውርደዋል።

የፈለጉትን ያገኙ የመሰሉት ጋዜጠኞች ኮንቴ ጣሊያን እያሉ በጨዋታ ውጤት ማጭበርበር ተከሰው እንደነበር ለጆሴ ሞሪንሆ ለማስታወስ ሲሞክሩ ጆሴ በበኩላቸው “እንደዛ አድርጓል?እኔ ግን አላደረኩም።” በማለት ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

በኤፍ ኤ ካፕ ከኖርዊች ጋር አቻ የተለያዩት ኮንቴ ከጨዋታው በኋላ”ሞሪንሆ ትንሽ ሰው ነው።” በማለት የቃላት ጦርነቱን ሌላ ቅርፅ እንዲኖረው አድርገውታል።

“ሁላችሁም በደምብ አድርጋቹ ታውቁታላችሁ።እሱ[ሞሪንሆ] ሁልጊዜ አይቀየርም።ይህ አስደናቂ ነገር አይደለም።የሆነ ሰው ስትሳዳብ ተሳዳቢው ትንሽ ሰው ነው ማለት ነው።ሞሪንሆም እነደዛው ትንሽ ሰው እንደሆነ አስባለው።

“ህይወት ይቀጥላል፣ዩናይትድን የምንገጥበት እለት ፊት ለፊት የምንገናኝበት ጥሩ አጋጣሚ ነው።እደግመዋለው እኔ ስለሌላ አሰልጣኝ ማውራት አልፈልግም።” ሲሉ ተደምጠዋል።

ቼልሲዎች በቻምፕየንስ ሊጉ ላይ ባርሴሎናን ከገጠሙ ከ አምስት ቀናት በኋላ የካቲት 25 ኦልድትራፎርድ ላይ ከዩናይትድ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ሁለቱ አሰልጣኞች ፊትለፊት ይፋጠጣሉ።

የሁለቱ አሰልጣኞች መካከል ባለፉት ጊዜያት የተደረጉ የቃላት ሽኩቻዎች

ጥቅምት 19 2017:”ሞሪንሆ የድሮ ክለቡን መመልከት ትቶ እራሱን መመልከት ይኖርበታል።” – ኮንቴ

ሀምሌ 29 2017: “የሞሪንሆን አይነት የውድድር አመት ማሳለፍ አይገባንም።” በማለት ኮንቴ በድጋሜ የፕሪምየርሊጉ ዋንጫን ለማግኘት እንደሚጫወቱ ተናገሩ።

 መጋቢት 14 2017: “እስካሁን ድረስ የአለም ቁጥር አንድ ነኝ።”ሲሉ ሞሪንሆ በኤፍ ኤ ካፕ በቼልሲ ከተሸነፉ በኋላ እኔ ከኮንቴ የተሻልኩ ነኝ የሚል ስሜት ያለው ንግግር በመናገር ኮንቴን በነገር ሸንቆጥ አደረጉ።

 የካቲት 12 2017:ሞሪንሆ ቼልሲ የመከላከል መንገድ እንደሚጠቀም ሲናገሩ ኮንቴ በበኩላቸው “የሞሪንሆን ቀልድ” አይመቸኝም ሲሉ ምላሽ ሰጡ።

ጥቅምት 23 2016:ቼልሲዎች ዩናይትድን 4-0 ካሸነፉ በኋላ ኮንቴ ባሳዩት የደስታ አገላለፅ “ማንንም ለማብሸቅ አይደለም።” ሲሉ ተናገሩ።

Advertisements