ፊሊፕ ኩቲንሆ / ሁሉም አካላት ያተረፉበትና መቋጫውን ለማግኘት የተቃረበው የብራዚላዊው ኮከብ ዝውውር ያልተሰሙ ዝርዝር ጉዳዮች

ሊቨርፑልና ባርሴሎና በፊሊፕ ኩቲንሆ ዙሪያ በ 160 ሚሊዮን ዩሮ ወይም 142 ሚሊዮን ፓውንድ ከስምምነት ላይ በመድረሳቸው ብራዚላዊው ኮከብ ዝውውሩን ለማጠናቀቅ ወደስፔን ለመብረር በዝግጅት ላይ መሆኑ ተነግሯል። 

ባርሴሎና ለቀያዮቹ ኮከብ ያቀረበውና በአንፊልዱ ክለብ ተቀባይነት እንዳገኘ የተነገረለት የዝውውር ሂሳብ በታላቋ ብሪታኒያ የዝውውር ታሪክ አንድ የብሪቴን ክለብ የቀረበለት እጅግ ትልቁ ሂሳብ ሆኖ የሚመዘገብ ሲሆን በስፔን ክለቦች በኩል የሚከፈል ትልቁ የዝውውር ሂሳብም ይሆናል።

የእንግሊዙ ተከባሪና ታማኝ ጋዜጣ የሆነው ቴሌግራፍ እንደፃፈው ለወራት የዘለቀው የብራዚላዊው ኮከብ የዝውውር ንትርክ ባርሴሎና የዝውውሩን አብዛኛውን መጠን በቅድሚያ ቀሪውን ደግሞ በማስያዣ በጊዜ ሂደት ለመክፈል በመስማማቱ በዛሬው ዕለት ቅዳሜ ከሰአት ላይ በሁለቱ ክለቦች መሀከል ከስምምነት ላይ መደረሱ ታውቋል። 

ይህ የኮቲንሆ የዝውውር ሂደት ሲጠናቀቅም የአንፊልዱ ኮከብ ባርሴሎና ለኔይማር ካወጣው የ 197 እና የፈረንሳዩ ፒኤስጂ ለክልያን ምባፔ ከከፈለው 160 ሚሊዮን ፓውንድ ቀጥሎ ሶስተኛው የአለም ውድ ተጫዋች ተደርጎ የሚቀመጥ ይሆናል። 

ሊቨርፑል ጉዳዩን በማስመልከት ያወጣው መግለጫም “ከባርሴሎና ጋር ከስምምነት ላይ በመደረሱ የሊቨርፑል እግር ኳስ ክለብ ፊሊፕ ኩቲንሆ የህክምና ምርመራውን ከፈፀመና ግላዊ ጥቅሞቹን የተመለከቱ ጉዳዮች ካጠናቀቀ በኋላ ክለቡን እንደሚለቅ ለማረጋገጥ ይወዳል። አሁን ተጫዋቹ የተለመደውን ሂደት እንዲፈፅምና ዝውውሩን በቶሎ እንዲያጠናቅቅ ፍቃድ ተሰጥቶታል።” ሲል ተነቧል።

በኒውካምፕ 400 ሚሊዮን ዩሮ የሚገመት የዝውውር ማፍረሻ ያለው የአምስት አመታት የውል ስምምነት እንደሚፈራረም የሚጠበቀው ኩቲንሆ በነገው ዕለት አመሻሽ ባርሴሎና ሌቫንቴን በሚያስተናግድበት ጨዋታ በስታዲየሙ ሊታደም እንደሚችል ተያይዞ ተገልጿል። 

የኩቲንሆ ዝውውር በታሰበው መልኩ መጓዙን የሚቀጥል ከሆነም የ 25 አመቱ ተጫዋች በመጪው ሰኞ ከአዲሱ ቡድኑ አባላት ጋር ልምምድ ማድረግ የሚጀምር ሲሆን የመጀመሪያ ጨዋታውንም በመጪው ማክሰኞ ባርሴሎና በኮፓ ዴላሬይ ከሴልታቪጎ በሚያደርገው ግጥሚያ ላይ ሊከውን እንደሚችል ተጠብቋል። 

ብራዚላዊው ኮከብ በትናንትናው ዕለት ምሽት ሊቨርፑል የምንግዜውም ተቀናቃኙን ኤቨርተን በረታበት ጨዋታ በጉዳት መሰለፍ ሳይችል የቀረ ሲሆን ቀደም ብሎም ለተወሰኑ ቀናት እረፍት ወደዱባይ ካመራው የቀያዩቹ ስብስብ ራሱን አግልሎ ቆይቷል። 

ይህ ተጠባቂ ዝውውር ባሳለፍነው ክረምት ባርሴሎና ኔይማርን ካጣ በኋላ ሊፈፅመው የሚፈልገው የነበረ ቢሆንም የአንፊልዱ ክለብ ባለቤት የሆነው ፊንዌይ ስፖርት ግሩፕ የተሰኘው ተቋም ተጫዋቹን በዛ የዝውውር መስኮት ለመሸጥ ፍቃደኛ ሳይሆን በመቅረቱ ሊንጓተት በቅቷል።

ከዛ ወዲህ ግን ሊቨርፑል በብራዚላዊው ኮከብ ዙሪያ ያለውን አቋም እያለሰለሰ የመጣ ሲሆን በዝውውሩ ድርድር ላይ በትልቁ የተሳተፈው የኩቲንሆ ወኪል ኪያ ጆራቢቻን ያመጣው የመግባቢያ እቅድ ለሁለቱ ክለቦች ከስምምነት ላይ መድረስ ስኬት በቀዳሚነት እየተጠቀሰ ይገኛል። 

በመጨረሻ የተደረሰበት ስምምነትም ሁሉንም አካላት ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑ እሙን ሆኖ የተገኘ ሲሆን መሀመድ ሳላህ በፊት መስመር ላይ የፈጠረው ትልቅ ተፅዕኖና ቡድኑ ሰይዶ ማኔን እና ሮበርት ፈርሚንሆን መያዙ እንዲሁም ደግሞ የአዳም ላላን ወደቀደመ የአካል ብቃቱ እየተመለሰ መሆኑ በኩቲንሆ ሽያጭ ሊቨርፑል ብዙም እንደማይጎዳ ማሳያ እንደሆነ ይታመናል።

ከዚህ በተጨማሪም የአንፊልዱ ክለብ የኩቲንሆን ወደ ባርሴሎና የማምራት ህልም በተመለከተ መንገድ ላይ መሰናክል ሆኖ መቆም ያልፈለገ ሲሆን በተለይም ደግሞ ለተጨዋቹ የፈለገውን ያህል የዝውወር ሂሳብና ስምምነቶች ማሳካት ስለቻለ የዝውውሩን መጠናቀቅ በአዎንታዊ መልኩ ተቀብሎታል። 

በሌላ በኩል ግን ሊቨርፑል ተጫዋቹን በማሳመን እስከመጪው ክረምት በአንፊልድ እንደሚያቆየው ተስፋ አድርጎ የነበረ ሲሆን በተለይ ደግሞ ተጫዋቹ ዘንድሮ ለባርሴሎና በቻምፒዮንስ ሊግ (በሊቨርፑል የዘንድሮ የቻምፒዮንስ ሊግ ስብስብ በመካተቱ) መሰለፍ የማይችል መሆኑና በቻምፒዮንስ ሊጉ ሁለቱም ክለቦች 16ቱን አላፊ ቡድኖች መቀላቀል መቻላቸው በ 25 አመቱ ተጫዋች ቆይታ ዙሪያ የቀያዮቹን ተስፋ የጨመረ ሂደት ነበር።

ሊቨርፑል የኩቲንሆን መልቀቅ አስመልክቶ ማረጋገጫ ከሰጠ በኋላም ጉዳዩን በማስመልከት አስተያየት የሰጡት የክለቡ ጀርመናዊ አለቃ የርገን ክሎፕ የብራዚላዊውን ተጫዋች ክለቡን መልቀቅ ከባድና የማይፈለግ አይነት ቢሆንም ለክለቡ ላበረከተው ነገር ምስጋና አቅርበው በአዲሱ ክለቡ መልካም ነገር እንዲገጥመው ተመኝተውለታል። 

ከኩቲንሆ ዝውውር ጋር በተያያዘ የወጡ መረጃዎችም ከቀናት በፊት በትልቅ የዝውውር ሂሳብ ተከላካይ ያስፈረመው ሊቨርፑል የ 25 አመቱን ብራዚላዊ የሸጠው የሂሳብ መዝገቡን ለማስተካከል እንዳልሆነና ከዚህ በተቃራኒው ተተኪ የሚሆነውን የጨዋታ አቀጣጣይ ለማግኘት በተለያዩ ተጫዋቾች ላይ ኢላማ መደገኑን አውስተዋል።

ከነዚህ ስማቸው ከሚጠቀስ ተጫዋቾች መሀከልም ባሳለፍነው ክረምት ሊቨርፑል ሊያስፈርመው የነበረውና በመጨረሻም በፈረንሳይ እንዲቀር ባይገደድ ኖሮ ወደ አርሰናል ሊያመራ የነበረው ቶማስ ሌማር ቀዳሚው ሲሆን ተጫዋቹ ወደአንፊልድ የማምራት ፍላጎት ሊኖረው እንደሚችል ነገርግን አርሰናል አሌክሲ ሳንቼዝን ሊያጣ የተቃረበ መሆኑና ሞናኮ አሁንም ተጫዋቹን የመልቀቅ ፍላጎት የሌለው መሆኑ ዝውውሩን እንዳያጨናግፈው ተፈርቷል። 

በሌላ በኩል ከፈረንሳይ እየወጡ ያሉ ዘገባዎች ሊቨርፑል የሌስተሩን ሪያድ ማህሬዝ ለማስፈረም እንቅስቃሴ ሊያደርግ እንደሆነ የሚያሳዩ ቢሆንም ሊቨርፑል በአልጄሪያዊው ተጫዋች ላይ ፍላጎት እንደሌለው የአንፊልድ ሁነኛ የመረጃ ምንጮች አስታውቀዋል።

Advertisements