ባርሴሎና ፍሊፔ ኮቲንሆን እንዴት ሊጠቀምበት ይችላል?

ባርሴሎና የፍሊፔ ኮቲንሆን ዝውውር ማጠናቀቁን ተከትሎ ተጫዋቹን እንዴት ሊጠቀምበት ይችላል የሚለው ቀጣይ ምላሽ የሚፈልግ ጥያቄ ሆኗል።ቡድኑስ ተጫዋቹን ለማሰለፍ ሲል የአጨዋወት ቅርፁን ሊቀይር ይችላል? በቀጣዩ መረጃ ባርሴሎና ተጫዋቹን ሊያሰልፍበት የሚችልባቸው አማራጮች ተዳሰዋል።

<!–more–>

ብራዚላዊው ፍሊፔ ኮቲንሆ ለአምስት አመት ከቀዮቹ ጋር ከቆየ በኋላ ክለቡን በመልቀቅ ዛሬ በከምፕ ኑ ተገኝቶ ከደጋፊዎች ጋር ተዋውቋል።

ሊቨርፑሎች 2013 ላይ 8.5 ሚሊየን ፓውንድ ያወጡበት ተጫዋች 142 ሚሊየን ፓውንድ ወደ ካዝናቸው በመክተት  ተጫዋቹን ለካታላኑ ቡድን አሳልፈው ሰጥተውታል።

ተጫዋቹ በአማካይ ቦታ ላይ በተለያዩ ቅርፆች መጫወት የሚችል በመሆኑ ባርሴሎናን በሚገባ መጥቀም እንደሚችል እየተነገረ ይገኛል።

በተለይ ደግሞ ወደ ግራ አዘንብሎ ሲጫወት ከሳጥን ውጪ አክርሮ የሚያስቆጥራቸው ኳሶች ለካታላኑ ቡድን ሌላው የተለየ ተጨማሪ የጎል ሀይል እንደሚሆንለት ይጠበቃል።

ኔይማርን ወደ ፒ ኤስ ጂ በማቅናቱ ምክንያት ትቶት የሄደውን ክፍተት ለመሸፈን ባርሴሎናዎች በቅድሚያ አይናቸውን የጣሉት በኮቲንሆ ላይ ነበር።

ኮቲንሆ እድሜው 25 በመሆኑ በቀጣዮቹ 5 አመታት በከፍተኛ ደረጃ ቡድኑን መጥቀም የሚችል ሲሆን በተለይ አንዳንድ የቡድኑ ተጫዋቾች የጨዋታ ጊዜያቸው ለማጠናቀቅ በመቃረባቸው እንደ ጨዋታዎች አይነት አንጋፋ ተጫዋቾች እረፍት በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ተክቶ በመግባት ሽፋን መስጠት ይችላል።

ተጫዋቹ በብዙ ቦታዎች ላይ መጫወት በመቻሉ ኮከቦች በተሰባሰቡበት የአለማችን ምርጡ ቡድን ውስጥ በየትኛው ቦታ ላይ መሰለፍ ይችላል የሚለው ከዝውውሩ ፍፃሜ በኋላ የሚነሳ ጉዳይ ነው።በዚህ ፁሁፍም ኮቲንሆ በባርሴሎና ሊሰለፍባቸው የሚችልባቸው አራት ቦታዎች በዝርዝር ቀርበዋል።

1) በ 4-3-3 የጨዋታ ቅርፅ[የኔይማር ተተኪ]

ባርሴሎናዎች በተጠቀሰው የጨዋታ ቅርፅ በግራ በኩል የማጥቃት እንቅስቃሴውን ባለፉት አመታት ሲመራው የነበረው ኔይማር በአለም የዝውውር ሂሳብ ወደ ፓሪስ ማቅናቱ ይታወሳል።

በክረምቱ የተፈፀመው ያልተጠበቀው ዝውውር ባርሴሎናዎች ምንም እንኳን ዳጎስ ያለ የዝውውር ሂሳብ ቢያገኙም የኔይማርን ትክክለኛ ተተኪ ማግኘት አልቻሉም።

በቦታው ላይ የተለያዩ ተጫዋቾችን እያፈራረቁ በማጫወት ላይ ቢሆኑም የኔይማርን ያህል ተፅእኖ መፍጠር የሚችል ተጫዋች ግን ማግኘት ሳይችሉ የውድድር አመቱን አጋምሰዋል።

ኮቲንሆ በባርሴሎና ሊሰለፍበት ከሚችልባቸው ቦታዎች ውስጥ ይኸው ኔይማር ሲጫወትበት የነበረው ወደ ግራ ያዘነበለው የአጥቂ ቦታ ነው።

በዚህ ቦታ ላይ የሚሰለፍ ከሆነ ደግሞ ከዚህ ቀደም የነበረው የ MSN [ሚሲ፣ስዋሬዝ፣ኔይማር] ጥምረት ወደ አዲሱ MSC [ ሜሲ፣ስዋሬዝ፣ኮቲንሆ] ጥምረት ይቀየራል።

ተጫዋቹ ከዚህ ቦታ ላይ ወደ ውስጥ ሰብሮ እየገባ የአጥቂ እንቅስቃሴውን ከማገዙ በተጨማሪ ጠንካራ ኳሶችን ማስቆጠር የተካነበት በመሆኑ በባርሴሎና ውስጥም በዚህ ቦታ ላይ እንግዳ እንደማይሆን ይጠበቃል።

2) 4-3-3 የጨዋታ ቅርፅ[የኢኔይስታ ተተኪ]

የባርሴሎና ባለስልጣኖች ኮቲንሆን ያዘዋወሩበት አንዱ ምክንያት የቡድኑ የረጅም ጊዜ ኮከቦች እሜያቸው እየገፋ በመምጣቱ በሁሉም ውድድሮች ላይ ለመጫወት የጉልበት እና የፍጥነት ውስንነት ስለሚኖርባቸው ተተኪ ለማዘጋጀት ነው።

በርግጥ ኮቲንሆ ኢኒየስታን ሙሉለሙሉ ይተካል ተብሎ ባይታሰብም ዘንድሮ በሁሉም ውድድሮች ላይ እየተፋለሙ ለሚገኙት ባርሴሎናዎች እንደ ጨዋታዎቹ አይነት ኢኒየስታን እያሳረፉ ኮቲንሆን እየተኩ የሚያጫውቱበት አጋጣሚ ተፈጥሮላቸዋል።

በተለይ ደግሞ ኮቲንሆ በቻምፕየንስ ሊጉ ላይ ለባርሴሎናዎች መሰለፍ የማይችል በመሆኑ ትኩረቱን በላሊጋው እና በኮፓ ዴልሬ በሚደረጉ የውስጥ ውድድሮች ላይ እንዲያደርግ በማድረግ ኢኒየስታን እየተካ እንዲጫወት እንደሚደረግ ይጠበቃል።

የ 33 አመቱ ኢኒየስታ ደግሞ በቻምፕየንስሊጉ ላይ ልምዱን ተጠቅሞ ቡድኑን እንዲያግዝ በሀገር ውስጥ ውድድሮች በኮቲንሆ እየተተካ በቂ እረፍት እንዲያገኝ ይደረጋል ተብሎ ይታሰባል።

በዚህ የ 4-3-3 የጨዋታ ቅርፅ ኮቲንሆ ዘንድሮ በሊቨርፑል እየተጫወተበት የሚገኝበት ከሶስቱ የፊት አጥቂዎች ጀርባ ያሉት ሶስት አማካዮች ውስጥ አንዱ በመሆን ወደ መስመር አስፍቶ የሚጫወትበትን እንቅስቃሴ በባርሴሎናም ሊጫወትበት የሚችለበት ሌላው ቦታው ነው።

በዚህ የጨዋታ እንቅስቃሴ ኮቲንሆ ከዴምቤሌ ጋር በአንድ ላይ የመጫወት አጋጣሚን የሚያገኝ እንደሚሆን ይጠበቃል።

3) 4-4-2 የጨዋታ ቅርፅ  [ ወደ መስመር ለጥጦ በመጫወት]

በዚህ የጨዋታ ቅርፅ ሜሲ እና ስዋሬዝ የማጥቃቱን እንቅስቃሴ በጋራ የሚመሩ ይሆናል።በአማካይ ደግሞ ሌሎች አራት ተጫዋቾች እንዲሰለፉ ይደረጋል።

 ኮቲንሆ ደግሞ ወደ መስመር ተጠግቶ ከአራቱ አማካዮች አንዱ ሆኖ መጫወት ይችላል።ነገርግን ምንም እንኳን ተጫዋቹ በዚህ ቦታ ላይ የመጫወት አቅም እንዳለው ቢታሰብም በደምብ የሚታወቅበት ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን መፍጠር እና ጎል በማስቆጠር በኩል ሊቸገር እንደሚችል ይጠበቃል።

4) 4-4-2 የጨዋታ ቅርፅ [የዳይመንድ ቅርፅ]

ኮቲንሆ በዳይመንድ የጨዋታ ቅርፅ ከስዋሬዝ እና ከሜሲ ጀርባ የዳይመንዱ የላይኛው ጫፍ ላይ በመሆንም መጫወት ይችላል።

በዚህ ቦታ ላይ የሚጫወት ተጫዋች ጥሩ እይታ ያለው፣በቴክኒክ የታደለ እና ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን የሚያመቻች ነው።

ኮቲንሆ ደግሞ በቦታው የሚፈለገው አሟልቶ ከመያዙ ባሻገር ጎልም ማስቆጠር የሚችል ተጫዋች በመሆኑ ለቡድኑ ሌላ ሊሰለፍበት የሚችለበት አማራጭ ይሰጠዋል።

በአጠቃላይ ባርሴሎና እንደ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ኤርኔስቶ ቫልቬርዴ የጨዋታ አቀራረብ ተጫዋቹን ከላይ ከተጠቀሱት አራት ቅርፆች በተለያየ መንገድ እያፈራረቁ የሚጠቀሙበት እድሎች አላቸው። 

Advertisements