እውነት ሀሰት / አልከሊፋ በፓውሎ ዲባላ እና ኡናይ ኤምሪ ዙሪያ ስለሚሰማው ጭምጭምታ ምላሽ ሰጡ 

የጁቬንቱሱ የፊት መስመር ኮከብ ፓውሎ ዲባላ የፒኤስጂ የዝውውር ኢላማ አለመሆኑን እና ኡናይ ኤምሪን አሰናብቶ በሌላ አሰልጣኝ የመተካት ሀሳብ እንደሌለ የፓሪሱ ክለብ ሊቀመንበር ናስር አልከሊፋ ገለፁ።

አርጀንቲናዊው ኮከብ ስሙ ከፈረንሳይ ሊግ አንድ ጋር ተያያይዞ የነበረ ሲሆን ባሳለፍነው ህዳር ወር ላይም ከኔይማር ጋር በጋራ የመጫወት እድል ቢያገኝ እንደሚወድ ያመነበትን መግለጫ መስጠቱ አይረሳም።

የዲባላ ብቃት ባለፉት ሳምንታት ከመውረዱ ጋር በተያያዘም ጁቬ ተጫዋቹን ለመሸጥ መፈለጉ እየተወራ የነበረ ሲሆን ከዚህ ጋር ተያይዞም ባርሴሎና፣ ሪያል ማድሪድ እና ማንችስተር ዩናይትድ ተጫዋቹን እንደሚፈልጉ ሲገለፅ ቆይታል። 

ነገርግን አልከሊፋ ከጣሊያኑ ጋዜጣ ላስታምፕ ጋር በነበራቸው ቆይታ “እውነታው በሴሪአው ዲባላ ብቻ ሳይሆን ብዙ ጥሩ ተጫዋቾች አሉ። እሱ ላይ ፍላጎት ካሳደርን ነገሩን ለጁቬንቱስ እናሳውቃለን።

“አጊኔሊ (የጁቬንቱሱ ፕሬዝዳንት አንድሬ አጊኔሊ) ጥሩ ጓደኛዬ ቢሆንም ልነግራችሁ የምችለው በዚህን ሰአት ዲባላ የፒኤስጂ የመጪው ጊዜ ቁልፍ እንዳልሆነ ነው።” በማለት ክለባቸው በ 24 አመቱ ተጫዋች ላይ ፍላጎት እንደሌለው የሚገልፅ አስተያየትን ሰጥተዋል። 

ከዲባላ ዝውውር በተጨማሪም የፓሪሱ ክለብ ሊቀመንበር ፒኤስጂ አሰልጣኙን ኡናይ ኤምሪን በሌሎች ለመተካት ነገሮችን እያጤነ እንደሆነ እየወጣ ያለው መረጃ ሀሰት መሆኑን ገልፀው ጉዳዩን ክደው ተናግረዋል።

ከሰሞኑ የፈረንሳዩ ክለብ ኤምሪን ለመተካት የቼልሲውን አንቶኒዮ ኮንቴ እና የቀድሞውን የክለቡን አለቃ ካርሎ አንቸሎቲ ለመቅጠር ማሰቡ በስፋት ሲወራ ሰንብቷል። 

አልከሊፋም “በጣም ምርጥ ተጫዋቾች፣ ምርጥ ክለብ እና ምርጥ አሰልጣኞች በጣሊያን አሉ። ነገርግን ለአሁኑ በኤምሪ ደስተኛ ነን።” በማለት በአሰልጣኙ ዙሪያ የሚወራውን ጭምጭምታ የሚያጣጥል አስተያየት ሰጥተዋል።

Advertisements