የተረጋገጠ / ፍሊፕ ኩቲንሆ ወደባርሴሎና የሚያደርገውን ዝውውር ቢያጠናቅቅም ለሳምንታት ከሜዳ ይርቃል

ፊሊፕ ኩቲንሆ የባርሴሎና ዝውውሩን ቢያጠናቅቅም በገጠመው ጉዳት ምክንያት ለሚቀጥሉት ሶስት ሳምንታት ለኒውካምፑ ክለብ ጨዋታ ማድረግ እንደማይችል ተገለፀ። 

የቀያዮቹ የቀድሞ ተጫዋች በ 142 ሚሊዮን ፓውንድ የአንፊልዱን ሊቨርፑል በመልቀቅ ወደስፔኑ ክለብ ያደረገውን ዝውውር በማጠናቀቅ በይፋ የባርሴሎና ተጫዋች መሆን ችሏል።

ነገርግን ብራዚላዊው ኮከብ ለባርሴሎና ለመፈረም ባደረገው የህክምና ምርመራ ወቅት የጭን ጉዳት ያለበት መሆኑ በመረጋገጡ ለ 20 ያህል ቀናት ከጨዋታ ውጪ እንደሚሆን ተያይዞ ተገልጿል። 

ከዝውውሩ መጠናቀቀ በኋላ የካታላኑ ክለብ ፕሬዝዳንት ጆሴ ማሪያ ባርቶሚዮ ለክለቡ ድረገፅ “ካሳለፍነው ክረምት አንስቶ ወደእኛ እንዲመጣና ለእኛ እንዲጫወት ስንሞክር የከረምነውን ተጫዋች (ፍሊፕ ኩቲንሆ) ወደመድረኩ አምጥተን ስናስተዋውቀው ትልቅ ደስታ ይሰማናል።” በማለት የተሰማቸውን ስሜት ገልፀዋል። 

ኩቲንሆ በበኩሉ “ይህ ዝውውር እውን እንዲሆን ያደረጉትን የክለቡን ፕሬዝዳንት እና ሌሎች አካላት ላመሰግን እፈልጋለሁ። በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ከዚህ ቀደም እንደተናገርኩት ይህ ነገር ህልሜ ነበር። በቀጣይ በሜዳ ላይ እንደምጠበቀው ሆኜ እንደምገኝ ተስፋ አደርጋለሁ።” ሲል በዝውውሩ መሳካት የተሰማውን ደስታ ገልጿል።

ኩቲንሆ ለሚቀጥሉት 20 ያህል ቀናት ከጨዋታ ውጪ የሚሆን ከሆነ አራት የላሊጋ ጨዋታና የኮፓ ዴላሬይ ፍልሚያ የሚያልፈው ሲሆን ብራዚላዊው ኮከብ ወደሜዳ እንደሚመለስ የሚጠበቀው በየካቲት ወር ባርሴሎና ከኢስፓኞል በሚያደርገው የደርቢ ጨዋታ ይሆናል። 

Advertisements