ፋይቅ ቦልኪያ – የዓለማችን ቱጃሩ እግር ኳሰኛ

እብደት የሚመስል የገንዘብ መጠን ለተጫዋቾች ወጪ በሚደረግበት በዚህ ዘመን የዓለማችን ሃብታሙ የእግር ኳስ ተጫዋች ማነው ? ለሚለው ጥያቄ የበርካቶች መልስ ከክርስቲያኖ ሮናልዶና ሊዮኔል ሜሲ አያልፍም፡፡ ግፋ ቢል እነኔይማር እነዝላታን ኢብራሒሞቪችንና ዌይን ሩኒን መጥቀስ የማይቀር ነው፡፡

እውነታው ግን ያ አይደለም ፤ የዓለማችን ቱጃሩ የእግር ኳስ ተጫዋች በእንግሊዝ ምድር ለሌስተር ሲቲ ሁለተኛ ቡድን እየተጫወተ ይገኛል ፡፡ ፋይቅ ቦልኪያ መጠሪያ ስሙ ነው፡፡

የፋይቅ አጎት የሆኑት የብሩናይ ሱልጣን

የብሩናይ ሱልጣን የሆኑት ሃሰናል ቦልኪያ የወንድም ልጅ የሆነው ተጫዋቹ በሃብት መጠኑ የሚወዳደረው ቀርቶ የሚጠጋው ተጫዋች የለም፡፡

የመስመር ተጫዋቹ ቦልኪያ የእንግሊዝ ቆይታውን የጀመረው በኒውበሪ ሲሆን ከዛ በኋላም በሳውዛምፕተን አርሰናል እና ቼልሲ አጫጭር ቆይታ ነበረው፡፡

የፋይቅ አባት የሆኑት ጄፍሪ ቦልኪያ በአንድ ወር ውስጥ ብቻ ለቅንጦት መኪኖች ፣ ሰአቶችና የወርቅ እስኪብርቶዎች እስከ 35 ሚልዮን ፓውንድ ወጪ እንዳደረጉ የተነገረ ሲሆን ከ 2300 በላይ ዘመናዊና የቅንጦት መኪኖች የተካተቱበት የመኪና ስብስብ አላቸው፡፡

ግለሰቡ የ 50ኛ አመት የልደት በአላቸውን ሲያከብሩ ለፖፕ ንጉሱ ማይክል ጃክሰን 12.5 ሚልዮን ፓውንድ በመክፈል ለዚሁ በአላቸው ባስገነቡት ስቴድየም የተወሰኑ የቅርብ ሰዎቻቸው ብቻ የታደሙበት ኮንሰርት ላይ ስራዎቹን እንዲያቀርብ ማድረግ የቻሉ ሰው ናቸው፡፡

የኚህ ቱጃር ልጅና ወራሽ የሆነው የሌስተሩ አማካይ እስከ 20 ቢልዮን ፓውንድ የሚገመት ሃብት ሲኖረው ከሱ አንፃርም የነሮናልዶና የነሜሲ የሃብት መጠን ኢምንት ነው፡፡

ከበርካታ የቢዝነስ አማራጮች በማፈንገጥ እግር ኳስን ምርጫው ያደሰገው ፋይቅ ስለዚሁ ጉዳይ ሲጠየቅ ቢተሰቡን በእጅጉ ያመሰግናል፡፡

“ከእፃንነቴ ጀምሮ ኳስ መጫወትን የምወድ ሲሆን ወደሜዳ ሄጄ እግሬን ከኳስ ጋር እንደማገናኘት የሚያስደስተኝ ነገር አልነበረም፡፡” የሚለው ቱጃሩ ፋይቅ ቀጥሎም “ቤተሰቦቼ ወደእግር ኳስ ተጫዋችነት በመለወጥ ሂደቴ ወስጥ ድጋፋቸው አልተለየኝም፡፡ በአካልም ሆነ በስነልቦና እንድዳብር ዘወትር ይደግፉኝ ነበርና ለኔ አርአያዎቼ ናቸው” ይላል የ19 አመቱ የሌስተር ሲቲ የመስመር አማካይ ቢልየነሩ ፋይቅ ቦልኪያ

Advertisements