በርሉስኮኒ ኤሲ ሚላን የሆድ ህመም እንደፈጠረባቸው ገለፁ

የቀድሞው የኤሲሚላን ፕሬዚዳንት ሲልቪዮ በርሉስኮኒ ኤሲ ሚላን እስካሁን ባሳየው የውድድር ዘመን ብቃት እንዳልተማረኩ ገልፃዋል።

ጣሊያናዊው የቢዝነስ ሰው በ2017 ክለቡን ለቻይናውያኑ የትብብር ድርጅት የሸጡት ቢሆንም፣ አዲሶቹ ባለቤቶች ምንም እንኳ ባለፈው ክረምት ለዝውውር ከ200 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ወጪ ቢያደረጉም ክለቡን ወደቀድሞው የጣሊያን እና አውሮፓ እግርኳስ ከፍታው መመለስ አልሆነላቸውም። 

ሮዞኔሪዎቹ አሰልጣኙን ቪንቼንዞ ሞንቴላን አሰናብተው በምትካቸው የክለቡን የቀድሞ ታሪካዊ ተጫዋች ጄናሮ ጋቱሶን በአሰልጣኝነት ቢሾሙም፣ ነገር ግን አሰልጣኙ ለመጨረሻ ጊዜ ማሸነፍ ከቻላቸው ሁለት ጨዋታዎች ውጪ በሴሪ አውም ሆነ በጣሊያን ዋንጫ ውድድሮች ላይ የተጠበቀውን ያህል ማድረግ አልተቻለውም። 

በርሉስኮኒም ከጣሊያኑ ራዲዮ ካፒታል ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የክለቡ ውጤት አሳሳቢ እንደሆነባቸው ተናግረዋል።

“ሁልጊዜም ኤሲ ሚላንን እደግፋለሁ። ነገር ግን እየተጫወቱ ያሉት በተሳሳተ ዘዴ ነው። ይህ ደግሞ የሆድ ህመም ፈጥሮብኛል። በአሁኑ ጊዜ ከውጭ ባለቤቶች ጋር መፎካከር የማይቻል ነው። እኔ ትልቅ ክለብ በባለቤትነት መያዝ አልችልም። ምክኒያቱም ዋጋው እጅግ ውድ ነው።  (ክለቡን የመሸጥ) ምርጫዬም የሚያሳምም ነበር። ነገር ግን የግድ አስፈላጊ ነበር።” በማለት በርሉስኮኒ ተናግረዋል።

ለአራት ጊዜያት ያህል ጣሊያንን በጠቅላይ ሚኒስቴርነት የመሩት የ81 ዓመቱ የሚዲያ ባለሃብት እና የፖለቲካ ሰው ሲልቪዮ በርሉስኮኒ በፎርብስ ጋዜጣ የ2017 መረጃ መሰረት 4.3 ሚሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት አላቸው።

Advertisements