የኢትዮጵያ ቡናና የጋቶች ፓኖም ድርድር ያለስምምነት ተቋረጠ

​በሩሲያው አንዚ ማካቻካላ ያደረገው ቆይታ ያለስኬት ከተጠናቀቀ በኋላ ወደአገሩ በመመለስ ለአሳዳጊ ክለቡ ለመጫወት ድርድር ሲያደርግ የቆየው ግዙፉ አማካይ በገንዘብ መጠን ባለመስማማቱ ድርድሩ መቋረጡን ክለቡ አሳውቋል፡፡



የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ እንዳሳወቀው አማካዩ ለአሳዳጊ ክለቡ ለመጫወት 250,000 ወርሃዊ የተጣራ ክፍያ በመጠየቁና ይህም የክለቡን አቅም ያላገናዘበ በመሆኑ ደርድሩን ለማቋረጥ ተገደዋል፡፡

ክለቡ እንደገለፀው ለተጫዋቹ ያልተጣራ(ታክስን ጨምሮ)130,000 ወርሃዊ ደመወዝ ለ 1 አመት ፊርማ ፣ ካልሆነም 150,000 ወርሃዊ ደመወዝ ለ 2 አመት ፊርማ ቢያቀርብለትም ተጫዋቹ የተሻሉ ጥያቄዎች እንደቀረቡለት በመግለፅ ጥያቄውን ውድቅ አድርጓል፡፡

ከሩሲያ መልስ ከክለቡ ዋና ቡድን ጋር ልምምዱን ሲሰራ የቆየው ጋቶች ምናልባት በስምምነቱ መሃል ከውጪ ክለቦች የዝውውር ጥያቄ ቢቀርብለት ክለቡ ሊያገኝ የሚገባውን ጥቅም ወደጎን በመተው እንዲሄድ እንደሚፈቅድለት ቢያሳውቅም ተጫዋቹ ግን በውሉ መማረክ እንዳልተቻለ ክለቡ ገልጿል፡፡

ጋቶች ቡናን የጠየቀው ገንዘብ በሩሲያ ሲጫወት ይከፈለው ከነበረው በሶስት እጥፍ የሚልቅ መሆኑን የገለፀው ክለቡ ይህም የክለቡን አቅም ያላገናዘበ ከመሆኑም በላይ በክለቡ ተጫዋቾች ላይ የሚያሳድረውን ስነልቦናዊ ችግር ከማስወገድ አንፃር ከተጫዋቹ ጋር ሲደረግ የነበረውን ድርድር ማቋረጡን አስታውቋል፡፡

Advertisements