ፊትለፊት / ሰፊ ቆይታ ከአቶ ተካ አስፋው ጋር (በተለይም ለኢትዮአዲስ ስፖርት)


ምስል : ከቢቢሲ ድረገፅ የተወሰደ

የዳሽን ባንክ ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑትና ለብዙ አመታት በተለያዩ ተቋማት ከህግ ጋር በተያያዘ የካበተ የስራ ልምዳቸው እንዲሁም ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ተቀዳሚ ፕሬዝደንትነታቸው የሚታወቁት አቶ ተካ አስፋው ከአራት አመታት በፊት ባልታወቀ ምክንያት በመጨረሻ ሰአት ራሳቸውን ያገለሉበትን የፌደሬሽን ፕሬዝዳንትነት ቦታ ለማግኘት ከሌሎች አራት ተፎካካሪዎቻቸው ጋር ለመፋለም አማራ ክልልን ወክለው ቀርበዋል። የኢትዮአዲሱ ሚኪያስ በቀለም ከሰሞኑ በአንዱ ቀን ሰመራ ላይ ቁርጡ ከሚታወቀው ምርጫ በፊት በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ከአቶ ተካ ጋር የሚከተለውን ቆይታ አድርጓል።


ኢትዮአዲስ : አቶ ተካ አሁን እግር ኳሱ ያለበትን ደረጃ እየተመለከትን ነው። ከሰሞኑ እንኳን በሴካፋ ትልቅ ችግር ውስጥ ገብቶ ታይቷል። እና ይሄን ቅርቃር ውስጥ ያለ እግር ኳስ መመልከት ምን ስሜት ይሰጦታል?

መልስ : እንግዲህ እንደ ሀገር እንደ ዜጋ የሚሰማህ ነገር አለ። በተለይ ደግሞ ለኳሱ ስሜት እና ፍቅር ሲኖር አገር ነውና ስሜቱ ከባድ ነው። ብሔራዊ ቡድኑ አሁን ባለበት ደረጃ እንደዚህ አይነት ውጤት ላይ ሲደርስ የሚሰማህ ነገር አለ። ያው የምልህ ሽንፈትን ማንም አይወድም። በተለይ ደግሞ ከጊዜ ወደጊዜ ውጤቱ እያሽቆለቆለ መሄዱ ደግሞ እጅግ የሚያሳዝን ነው። በዚህ የተነሳም በጣም ነው የማዝነው። ዞሮዞሮ ግን የማን ውጤት ነው? ለምን ሆነ? የሚለው እኔ የምመልሰው ነገር አይደለም። እንግዲህ የብዙ ነገር ድምር ውጤት ነው። የብሄራዊ ቡድን ውጤት ማሽቆልቆል ወይም መሸነፍ የብዙ ድምር ውጤት ነው ብዬ ስለማምን ነው። በአጠቃላይ ግን ስሜቴ ጥሩ አይደለም። በተለይ ከሴካፋ እንደዚህ አይነት የወረደ ነገር ታይቶ አይታወቅም። በሴካፋ በአራት ለምናምን የተሸነፈበትን ጊዜ አላስታውስም። ያውም በብሩንዲ ብሄራዊ ቡድን። እና ይሄ የሚመስለኝ ለእኛ በጣም ሞት ነው። እና ኢትዮጵያ አሁን ያላት የእግር ኳስ ውጤት ጥሩ አይደለም። እንዴት ነው የሚለወጠው? እንግዲህ ወደፊት የምናየው ይሆናል።  

ኢትዮአዲስ : እርስዎ ብዙ ጊዜያት እግር ኳስን መውደድዎት እና ከዚህ ቀደም አመራር ላይ ሳሉ በፕሮሞሽንና ማርኬቲንግ ላይ ብዙ ግልጋልዎት መስጠትዎን ወደፌደሬሽኑ ለመመለስ እንደ ምክንያት ሲያነሱት ይታያል። እነዚህ ምክንያቶች ግን ፌደሬሽኑን ለመምራት በቂ ናቸው ብለው ያስባሉ? 

መልስ : አይ! አይ! በቂ ነው ብዬ አላስብም። በእርግጥ ምንአልባት ብዙ ከተናገርኩት ውስጥ ይሄ ጎልቶ ታይቶ ይሆናል። ግን እሱ ካሉኝ ምክንያቶች አንዱ ነው የሚሆነው። በመጀመሪያ ደረጃ እግር ኳስ ብዙ ነገር ነው። እግር ኳስ ውጤት ይፈልጋል። በውጤት የታጀበ እንዲሆን ደግሞ ጥሩ ስራ ያስፈልጋል። ጥሩ ለመስራት ደግሞ መሰረታዊ እቅድ ያስፈልጋል። ያውም ዘመናዊ የሆነ እቅድ ያስፈልጋል። የዘመነ እቅድ አሰፈላጊ ነው። መነሻው መሆን ያለበት እሱ ነው። ገዢ የሚሆነውም እሱ ነው። ስለዚህ ከዚያ በኋላ የእቅዱ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን አደረጃጀቱ በአጠቃላይ የፌደሬሽኑ አደረጃጀት የጠቅላላ ጉባኤው አደረጃጀት መፈተሽ አለበት። መተዳደሪያ ደንቡ ይሄ ነው።

እንግዲህ አደረጃጀት የሚባለው ደግሞ ሌላው የአሰራር ሂደት ነው። አሰራሩ ደግሞ ምንድነው? ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለው አሰራር ነው። እየሄድን ያለነው በዘፈቀደ ነው? አሁን እየሄድንበት ያለነው አሰራር ግልፅነት የሰፈነበት ነው? ተጠያቂነትስ አለበት? እሱ መፈተሽ ያለበት ይመስለኛል። አመራሩስ? እንግዲህ ለአንድ ተቋም መፈተሽ ያለበት ነገር አደረጃጀት፣ አመራር እና አሰራር ነው። ስለዚህ አመራሩስ ምንድነው? ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው? የሚለው ነገር ይታያል። በዚህ ጥላ ስር ትሆንና አደረጃጀት ምን ማለት ነው? የሚለው ላይ ትኩረት ታደርጋለህ። አደረጃጀት የምንለው ፅህፈት ቤቱ በደንብ መደራጀት አለበት። እራሱን ችሎ መስራት መቻል አለበት። ስራ አስፈፃሚው ደግሞ ከውድድር መውጣት አለበት። 

የሊግ ውድድር ላይ የክለቦችን የሊግ ውድድር ለክለቦች ሊግ ማስረከብ አለበት። የፌደሬሽኑ አመራር እንደ በላይ አመራር ስትራቴጂክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ፣ መመሪያና አመራር መስጠት፣ የመገምገምገም ቆጥሮ የሰጠውን ቆጥሮ የመረከብ ስራ መስራት አለበት። ካልሆነ ግን ቢሮ ተቀምጦ እያንዳንዱ ማመልከቻ ላይ እየመራ መቀጠል ካሰበ ውጤቱ አሰልቺ የተለመደው የዕለት ተዕለት ስራ ውስጥ ገብቶ መዳከር ነው። የዕለት ተዕለት ስራ ደግሞ የትም ሊያደርሰን አይችልም። አንዱ ይሄ ነው። ስለዚህ የፅህፈት ቤት ሀላፊውን እንዲበቃ (empower) አድርጎ ስራውን የሚሰራበትን መንገድ መምራት ከዛ በኋላ ቀጣዩ ነገር የሚሆነው በሪፖርት ደረጃ ክንውኑን መገምገም ነው። 

ሌላው ነገር ደግሞ የቴክኒካል ክፍሉ ነው። ቴክኒካል ክፍል የምንለው ነገር ብዙ ነው። ያው እንግዲህ ውስጡ የሴቶች ጉዳይ፣ የታዳጊ ወጣቶች (grassroot) አለ። ይሄ ሁሉ በቴክኒካል ክፍል የሚካተት ነው። ያንን በበቂ ባለሙያ የማደራጀት ስራ ነው። እና ሂደቱ ስራን ከፋፍሎ የመስጠት ነገር ነው። በሌላ በኩል የሚደራጀው የዚህ የዳኝነት አካሉ ነው። የዳኝነት አካሉ አሁንም ቢሆን የሌሎች ሀገሮች፣ የካፍም ሆነ የፊፋም ተሞክሮ የሚያሳየን ራሱን የቻለ የዳኝነት ክፍል አለ። እሱን በደንብ አጠናክሮ በዳኞች ላይ ጠንካራ ስራ የሚሰራበትን መንገድ ማከናወን ማደራጀት ነው። 

ሌላው ቅድም ያነሳኸው የስፖርት ገንዘብ ነው። ያለገንዘብ ስፖርት ማከናወን አትችልም። ገንዘብ ለማግኘት ደግሞ የንግድ እና ማስታወቂያ (marketing and promotion) ስራ ወሳኝ ነው። ስለዚህ ይሄንንም ክፍል በተጠና ሁኔታ፣ ዘመናዊ በሆነ ሁኔታ ተደራጅተው እና በተቻለ መጠን ፌደሬሽኑ ከጥገኝነት የሚወጣበትን ነገር መፍጠር ነው። ሁልጊዜ በጣም በርካታ ነገሮች ከተሰሩ በርካታ ነገሮች መስራት ይቻላል። እናም በዛ ዙሪያ የገንዘብ አቅማችንን የማጠናከር ስራ መስራት ነው። አሁን የሴቶቹም የወንዶቹም ብሔራዊ ቡድን ውጤት ላይ እያየነው እንዳለነው ሁለቱም ጥሩ አይደለም። እሱን እንዴት መለወጥ ይቻላል? መሰረታዊው ነገር ሶስት እቅድ ይሄ እገባለሁ ብዬ አስባለሁ። 

የመጀመሪያው የአጭር ጊዜ እቅድ ነው። የአጭር ጊዜ የሚባለው አሁን ካለንበት የሴካፋ ደረጃ ላይ ያለን ውጤት ከምስራቅና መካከለኛ አፍሪካ ቡድኖች የተሻለ ሆኖ መገኘት ነው። እዛ አካባቢ ካሉ ሀገሮች በተሻለ ሆኖ የመገኘትን ነገር የመስራት ስራ ነው። የመካከለኛ ጊዜ የምንለው ደግሞ ቢያንስ እነዚህ አብረውን መስራች ናቸው ከምንላቸው እንደ ግብፅ ካሉ ሀገሮች ጋር የተቀራረበ ውጤት እንዲኖረን የማድረግ ውጤት ነው። ይህም ማለት ከነዛምቢያ አይነት የደቡብ ዞን ቡድኖች ጋር መፎካከር የሚያስችለን ውጤት ነው። ሌላው የከፍተኛ ደረጃ እቅድ የምንለው የምዕራብ እና ሰሜን አፍሪካ ቡድኖች የደረሱበት ደረጃ እግር ኳሳችንን ማድረስ ነው። ያ ማለት እንግዲህ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍን ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ መግባትን ይጠይቃል። 

ግን እዚህ ላይ ጥያቄው ይሄ እንዴት እውን ይሆናል ነው። ስላልን፣ ስለፈለግን፣ ስለተናገርን አይደለም። አንደኛ መሰረት መጣል ያስፈልጋል። በትምህርት ቤቶች አካባቢ ትልቅ ስራ መሰራት አለበት። ሰፈር አካባቢ እና ታዳጊ ፕሮጀክት ላይ መስራት ያስፈልጋል። ታዳጊ ፕሮጀክት ላይ መስራት ካለብን ደግሞ እጅና ጓንት ሆኖ መስራት ያስፈልጋል። እነጊዮርጊስ የጀመሩት ነገር አለ። በግል ደረጃ እነሰውነት ቢሻው፣ ነፍሱን ይማረውና እነአሰግድ ተስፋዬ የጀመሯቸውን የማገዝ ስራ ሊኖር ይገባል። በገንዘብ እንኳን ባይሆን በባለሙያ እና ቁሳቁስ በመስጠት የማገዝ እና ውጤት ላይ እንዲደርሱ የማረግ ስራ ያስፈልጋል።

ክለቦችን በተለይ አመራራቸው አካባቢ የማብቃት ስራ መስራት፣ ክክለብ አመራሮች ጋር ጥልቅ የሆነ ስራ የመስራት፣ ከክልል ፌደሬሽኖች ጋር በታዳጊ ፕሮጀክት ላይ እንዴት ነው የሚሰራው? በሚለው ላይ ትኩረት ማድረግ አንዱ ነው። ከትምህርት ሚኒስትር ጋር ሰፊ ስራ የመስራት ነገር ሌላኛው አስፈላጊ ነገር ነው። ይሄም ብቻ ሳይሆን ደግሞ ፊፋ የፈቀደው የጎል ፕሮጀክት አለን።አምቦ ላይ ያለውና የማንጠቀምበት የሴካፋ ማሰልጠኛ ተቋም የተባለውስ እጣፈንታው ምንድነው? እሱ ላይ መወሰንና በዚህ ዙሪያ ላይ በርካታ ስራዎችን መስራት ይቻላል። በአጠቃላይ ውጤት የምንፈልግ ከሆነ በወንድም በሴትም ከታች ጀምሮ አሰራር ዘርግተን መንቀሳቀስ አለብን። 

ኢትዮአዲስ : አሁን እርስዎ በእቅድ ደረጃ ያነሷቸውን ነገሮች ለመፈፀም ግን አሁን ያለው የፌደሬሽኑ የስልጣን ቆይታ የሚፈቅድ አይነት አይደለም። እና እንዴት ያዩታል ይሄንንስ? 

መልስ : ይሄን ነገር የምታየው በሁለት መንገድ ነው። አንድ የኔ አመለካከት የሚመጣው አመራር ቢያንስ ሁለት የስልጣን ዘመን (ስምንት አመት) መስራት አለበት። ይሄን የምለው በሁለት ምክንያት ነው። አንድ በአለም አቀፍ ሊኖረን የሚገባንን ቦታ እያጣን ነው። በየአመቱ አዳዲስ አመራር ሲመጣ እርስበርሳችን እየተጠላለፍን እየወደቅን ነው። በካፍ ደረጃ ያለንን ነገር ማስመለስ አለብን። ሌላው አንድ አመራር የጀመረውን ስራ ጨርሶ መሄድ አለበት። በስምንት አመት ብዙ መስረት መጣል ይቻላል ብዬ አስባለሁ። ዋናው መሰረት የመጣል ጉዳይ ነው። በአራት አመት ውስጥ መሰረት እንጥላለን ማለት የዋህነት ነው። አንድ አመቱ እኮ የሚያልቀው በጥናት ነው። ከዛ ሁለት አመቱ ደግሞ ሂደት ውስጥ በመግባት ያልቃል። ሶስተኛ አመት ሲመጣ ደግሞ ወደ ምርጫ ትዞራለህ። ያ ማለት ግን አመራሩ ከነችግሩ ይቀጥል ማለቴ አይደለም። አዲስ አመራር ስናመጣ ኢላማ ማድረግ ያለብን ለአራት አመት ሳይሆን ለስምንት አመት ሊሰራልን እንደሚችል በማሰብ ይሁን ለማለት ነው። 

ኢትዮአዲስ : እስቲ ከላይ የነገሩኝን እቅዶች የአጭር ጊዜ፣ የመካከለኛ እና የከፍተኛ ብለው በጊዜ ከፋፍለው ያስቀምጡልኝ። 

መልስ : አጭር ጊዜ የተባለው ሁለት አመት ነው። በዚህ ውስጥ በሴካፋ የነበረንን አቅም መመለስ እና ባሉን ተጫዋቾች የፌፋ ወርሀዊ ደረጃችንን ወደነበረበት ማስመለስ ነው። መካከለኛ የሚባለው በአራት እና አምስት አመታት ባለው ጊዜ የተሻሉ የተባሉት የደቡብ አፍሪካ ዞን እነደቡብ አፍሪካ አይነት ቡድኖች ጋር የመድረስ ነው። መጨረሻ ላይ ግን በስምንት አመት ጊዜ ውስጥ ወደምዕራብና ሰሜን አፍሪካ ቡድኖች መድረስ ነው። ይህን ደግሞ ከዚህ ቀደም በነበረው የስልጣን ዘመኔ ማሳካት ችለናል። ያኔ ውጤት የመጣው ከስር ስለተሰራ አልነበረም። ባሉን ተጫዋቾች በአግባቡ ስለተሰራ የመጣ ውጤት ነው። 

ኢትዮአዲስ : እዚህ ላይ ግን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ችግር የሜዳ ላይም ከሜዳ ውጪም (የአስተዳደርም) ነውና። ሁለቱን ጉዳዮች ትኩረት ሰጥቶ መጓዝና ችግሮቹን በአንዴ መቅረፍ ይቻላል?

መልስ : ማስኬድ ይቻላል። አመራሩ ሁሉንም ተሸክሞ መሄድ ስለሚፈልግ እንጂ ስራ ከፋፍለህ ከሰጠህ ይቻላል። 

ኢትዮአዲስ : ይሄን የምሎት በእግር ኳሱ ላይ ከሰፈነው ግለኝነት አንፃር እርስዎ የሚሉት ነገር ትልቅ እንደ ቡድን የመንቀሳቀስ ሂደትን ስለሚፈልግ ብዬ ነው።

መልስ : የጋራ አመራር ነው። ሳወራም ብቻዬን እሰራዋለሁ ብዬ ሳይሆን የጋራ አመራሩን ግምት ውስጥ ከትቼ ነው። ዞሮዞሮ ግን አደረጃጀትህን ማየት ያለብህ እንደ አመራር አቅጣጫ መስጠት ላይ ነው። የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮም የሚያሳየው ይሄንን ነው። ትልቁ ችግር ሁሉንም እኛ እንሰራዋለን ካልን ችግር ይመጣል። ለሁሉም የራሱ ባለቤት ሊኖረው ይገባል። ባለቤት ካለው ቆጥረህ እየሰጠህ በወር አንዴና ሁለቴ እየተገናኘህ ትገመግማለህ። ስራ የማይሰራልህ ላይ ርምጃ ትወስዳለህ። እንደዛ እያረክ መሄድ አለብህ። አለም አቀፍ ሀገራት ላይ እኮ ፌደሬሽኖች የሚመሩት በፅህፈት ቤት ሀላፊው ነው። ኢንፋንቲኖ እኮ ቢሮ ሆኖ ስራ እየሰራ አይደለም። የምትሰራው ዋና ፀሀፊዋ ናት። ኢሳ ሀያቱ ያንን ቢሮ ሲመሩት የነበሩት ቢሮ ተቀምጠው አይደለም። ዋና ፀሀፊውን የማብቃት ጉዳይ ነው። እሱን መስራት ነው።

ኢትዮአዲስ : አሁን እኮ ችግሩ እርስዎ እንደ ተሞክሮ የሚያነሱልኝ ሀገራት የጠነከረ ተቋማዊ አደረጃጀት አላቸው። እኛ ደግሞ ግለሰብ በመጣና በሄደ ቁጥር የሚቀያየር ተቋማዊ ቅርፅ የሌለው አካሄድ የሌለን ነን።

መልስ : ልክ ነህ እሱን መፍጠር ያስፈልጋል። አደረጃጀት ያልኩህ ለዛ ነው። ቅድም ሶስት መሰረታዊ ነገር አንስቻለሁ። አደረጃጀት፣ አሰራር እና አመራር ብያለሁ። ሀላፊነቱን ለፅህፈት ቤት ሀላፊው ከተጠያቂነት ጋር ትሰጠዋለህ። ከዛ ትገመግመዋለህ እንዲሁም ትከታተለዋለህ። የቴክኒክ እና የዳኝነት ክፍሉንም እንደዚሁ ታደርገዋለህ። ስልጣንህን በውክልና ካልሰጠህ አማተር መሆንህ ቀርቶ ተቀጣሪ ሰራተኛ ትሆናለህ። አንዱ ማነቆ ይሄ ነው። ስራ አስፈላሚው በሁሉም ስራ እየገባ ነው። ደብዳቤ መምራት የእነሱ ስራ ሳይሆን ደብዳቤ ይመራሉ። አሰራሩን አንዴ ከዘረጋኸው ይስተካከላል። ቅድም እንደተናገርከው ዋናው አሰራር መዘርጋት ነው። አመራር ከአመራር ሊቀያየር ይችላል። እኔ የሚገባኝ አሰራር እስካለ ማንም ይምጣ ማን ያለምንም ችግር መሄድ እንደሚቻል ነው።

ኢትዮአዲስ : ሌላው ደግሞ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑን ፕሬዝዳንትነት እንደ ትርፍ ጊዜ የመመልከት ነገር ይታያል። ግን እውነት እንደዚህ አይነት ችግር ውስጥ ያለን እግር ኳስ በትርፍ ጊዜ ስራነት ተይዞ ከህመሙ ማዳን ይቻላል?

መልስ : አማተር አገልጋይ በየትም ሀገር አለ። ወደእኛ ሀገር ስናመጣው ግን እያንዳንዱ ስራ ላይ ጣልቃ እንገባለን። የምመጣው ያንን ለማስተካከል ነው። ያንን እስክታስተካክል ድረስ እዛ ውስጥ ትዘፈቃለህ። ቶሎ መውጣት ግን አለብህ። እንደገባህ ይህን አሰራር እስክታዋቅር አጣብቂኝ ውስጥ ልትገባ ትችላለህ። ብዙ መስዋዕትነት መክፈል አለብህ። የምትገባው እኮ ዝም ብለህ አራት አመት ቆጥረህ ለመውጣት አይደለም። እኔ ችግሩን አውቀዋለሁ ችግሩን ለመፍታት ጊዜ አይወሰድብኝም ባይ ነኝ። በአጠቃላይ ወዲያው ፈጣን በሆነ ሁኔታ ከችግሩ ባንወጣም በተወሰኑ ጊዜያት ውስጥ ከተለመደው አሰራር እንወጣለን ነው።

ኢትዮአዲስ : ይህ ምርጫ ፖለቲካዊ ነው?

መልስ : በመሰረቱ ምግብ እራሱ ፖለቲካ ነው።

ኢትዮአዲስ : ጥያቄውን ግልፅ ላርገውና ምርጫው የመንግስት ጣልቃገብነት አለው ወይ?

መልስ : አሁን እሱን መናገር አልችልም። መንግስት ጣልቃ ገብቷል አልገባም የሚለውን መናገር አልችልም።

ኢትዮአዲስ : እሺ አንዳንድ ቦታ ላይ እርስዎ ከመንግስትም ድጋፍ እንዳሎት የሚፃፉ ነገሮችም አሉ። በእሱ ጉዳይ ላይስ ምን ይላሉ?

መልስ : አንቀላቅለው። እኔን የወከለኝ የአማራ ክልል ነው። ያንን ለማለት ተብሎ ከሆነ ልክ ነው።

ኢትዮአዲስ : እሱማ ሁሉም ተወካይ ለምርጫ የቀረበው በክልል ውክልና ነው። 

መልስ : መንግስት ከተባለ እሱ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ እኔ የፖለቲካ ድርጅት አባል አይደለሁም። እኔ የፖለቲካ ሰው ሳልሆን የሙያ ሰው ነኝ። እኔ የህግ ባለሙያ ነኝ። ለስፖርቱ ትልቅ ፍቅር አለኝ። ከአሁን በፊት ውጤት አሳይቼ (ከእግር ኳስ አመራሩ) ወጥቻለሁ። እኔ ከፖለቲካ ጋር ግንኙነት የለኝም። 

ኢትዮአዲስ : ስለዚህ እዚህ ምርጫ ውስጥ ፖለቲካዊ ጣልቃገብነት የለም ብለው ነው የሚያስቡት? 

መልስ : አላውቅም። እኔን በሚመለከት በእርግጠኝነት የምነግርህ፣ በእርግጠኝነትም ብቻ አይደለም 200 ፐርሰንት ሆኜ የምነግርህ የእኔ ውክልና ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ ውክልና የለውም። ግልፅ አድርጌ የምነግርህ የህዝብ ውክልና ነው። የህዝብ ውክልና ደግሞ የስፖርትና ስፖርቱን ብቻ መሰረት ያደረገ ነው። ይህን አረጋግጥልሀለሁ። የሌሎቹን መናገር አልችልም። አሁን አንዳንዶቹ ከእኔ ጋር የሚወዳደሩ ሰዎች ‘እኔ ፖለቲከኛ ነኝ’ ይላሉ። ‘የመንግስት ሀላፊነት ተሰተጥቶኝ፤ መንግስት ግባ ብሎኝ’ ይላሉ። እኔ አላልኩም። በመንግስት ስም እየተነገደ ነው? እኔ አላውቅም። ትክክለኛ ውክልና ሰጥቷቸው ነው? እሱን መመለስ ያለባቸው እነሱ ናቸው። 

እኔ ግን የማረጋግጠው በመጀመሪያ ደረጃ የመንግስት ሰው መሆን ወንጀል አይደለም። ግን እውነታው ምንድነው? መንግስት እያለ ያለው እኮ እንደውም ምርጫው ነፃ ይሁንና ውድድሩ ይካሄድ ነው። እርስበርሳችሁ ጉዳዩን ፍቱት ነው። አንዳንድ ባለስልጣኖች እጃቸውን አላስገቡም? እሱ ምንም ጥያቄ የለውም ምልክቶች ይታያሉ። የመንግስት አቋም ነው ወይ? ብዬ አላስብም። የግለሰቦችን እና የመንግስትን ፍላጎት መለያየት ያስፈልጋል። ያለውን መከራ፣ ስቃይ፣ ስም ማጥፋቱ፣ አሉባልታው እንደምታየው ነው።  ህጎች እየተጣሱ ነው። ይህን መንግስት ማስቆም ነበረበት? ከቆመ ማስቆም ነበረበት። 

በአጠቃላይ ግን እኔ ለስፖርቱ ንፁህ የሆነ ፍቅር አለኝ። ወደዚህ የመጣሁት እሱን ለመታደግ ነው። ስመጣ ገንዘቤን፣ ጊዜዬን ለማባከን ጭምር ተዘጋጅቼ ነው። ለስፖርቱ ዋጋ መክፈል ስለፈለኩ ነው። ፍቅሩም ስላለኝ ነው። መስዋዕትነት ብቻ ሳይሆንም ለውጥ እንደማመጣ ስለማምን ነው። ከዚህ ውጪ ከጀርባዬ ምንም የለም። ፖለቲካ በሉት ምን በሉት እኔን አይመለከተኝም። 

ኢትዮአዲስ : ከአራት አመት በፊት ከተፈጠረው (ራሳቸውን ከፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ካገለሉበት) በተቃራኒው እስከመጨረሻው ለመጓዝ ቁርጠኛ ኖት?

መልስ : አዎ። 100 በመቶ ቁርጠኛ ነኝ። 

ኢትዮአዲስ : ሌላው ደግሞ ፌደሬሽኑ ከሚዲያ አካላት ጋር ያለው የተቃርኖ ግንኙነት ነው። በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ጋር ጥሩ ግንኙነት የለውም። ትችት የሚፈራና ከሚዲያው ጋር ሰላማዊ ግንኙነት የሌለው ነው። ይህን በሚመለከት ምን ሀሳብ አሎት?

መልስ : ያን ጊዜ በአመራር ላይ በነበርኩበት ጊዜም ከሚዲያ ጋር ጥሩ ግንኙነት ነበረኝ። ይሄ የመፈለግ ያለመፈለግ ጉዳይ አይደለም። ይሄ ግዴታ (ከሚዲያ ጋር ጥሩ ግንኙነት የመመስረት) እንጂ በግለሰቦች ስሜት የሚነዳ ነገር አይደለም። ለምን እንፈራቸዋለን? እናክብራቸው። ሙያውን እናክብረው። መጀመሪያ አስተሳሰባችን መቀየር አለበት። ሚዲያ ሁልጊዜም እንደ ወቃሽ እንደ ነቃሽ ከተቆጠረ እሱ አያስማማንም። መጀመሪያ ሚዲያውን በአዎንታዊ መልኩ ተመልክተን ማየት ያለብን እንደ አጋዥ ነው። ከስርዓት ሲያፈነግጥም ሚዲያው የሚጠየቅበት ህግ አለ። ከዚህ ውጪ ግን ከሚዲያ ጋር ሌላ የተለየ ነገር የለም። የተለየ ፍቅርም አያስፈልግም። ስራው ያገናኝሀል። በስራው ትገናኛለህ፤ በስራው ትወያያለህ አበቃ።

ኢትዮአዲስ : በመጨረሻ እስቲ ያልዎትን መልእክት ያስተላለፉ።

መልስ : ስፖርት የሁሉም ስራ ነው። ስለዚህ ስራ አስፈፃሚው የሚመራው ስራ ብቻ አይደለም። እግር ካሱ የብዙ ፍላጎት ድምር ውጤት ነው። ስለዚህ ይሄ ሁሉ ፍላጎት እስካለ ድረስ አብሮ በጋራ መስራት ይጠይቃል። አብረን በጋራ እንስራ ብዬም ጥሪዬን አስተላልፋለሁ። 

Advertisements