ቆይታ / አንድሬ ክርስቲንሰን እስከ 2022 በቼልሲ የሚያቆየውን አዲስ የውል ስምምነት ተፈራረመ

የቼልሲው ወጣት ተጫዋች አንድሬ ክርስቲንሰን እስከ 2022 ድረስ በስታምፎርድ ብሪጅ የሚያቆየውን አዲስ የውል ስምምነት ተፈራርሟል። 

የ 21 አመቱ ተጫዋች በአንቶኒዮ ኮንቴ በሶስት ተከላካዮች የተዋቀረ የአጨዋወት መንገድ ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዴቪድ ሊውዝን ከቋሚ አሰላለፍ ውጪ በማድረግ ቁልፍ ሚናን እየተወጣ ሲሆን በሰማያዊዎቹ መለያም 22 ጨዋታዎችን ማድረግ ችሏል። 

ዴንማርካዊው ኮከብ ብሮንድባይን በመልቀቅ በ 2012 ቼልሲን የተቀላቀለ ሲሆን ከሶስት አመታት ቆይታ በኋላ በ 2015 ፕሮፌሽናል ውል ከመፈራረሙ በፊትም በሰማያዊዎቹ የወጣት ቡድን ውስጥ ብቃቱን ሲያሳድግ ቆይቷል።

ክርስቲንሰን ወደቦርሲያ ሞንቹግላድባ በውሰት በማምራት በነበረው ቆይታም እራሱን ማጠንከር የቻለ ሲሆን በጀርመኑ ክለብ ቆይታውም በሁሉም ውድድሮች ላይ በቋሚ ተሰላፊነት 83 ጨዋታዎችን ማድረግ ችሏል። 

ከስምምነት ማራዘሚያው በኋላም “አዲስ ውል መፈረሜ እና ለቼልሲ ታማኝ መሆኔ አስደስቶኛል። በቼልሲ ብዙ ጨዋታዎችን ማድረግ ችያለሁ። በክለቡ ቆይታዬ ደስተኛና ሁሉም ነገር በጥሩ ሁኔታ እየሄደልኝ ነው።” በማለት በስታምፎርድ ብሪጅ ያለውን ቆይታ በማራዘሙ የተሰማውን ደስታ ገልጿል።

ቼልሲ በውሰት ከመስጠት ጋር ባለው አሰራር ተደጋጋሚ ትችት የሚደርስበት ሲሆን ብዙ ቁጥር ያላቸው ታዳጊዎችም በትልቅ ተስፋ ውስጥ ሆነው ወደስታምፎርድ ብሪጅ ቢመጡም ልምድ እንዲያገኙ በሚል በውሰት ተሰጥተው በብዙ አጋጣሚ ወደ ክለቡ ሳይመለሱ በዛው መቅረታቸው አይረሳም። 

ነገርግን ክሪስቲንሰን ይሄንን ልማድ በመስበር ከቦሩሲያ ፓርክ ቆይታው ትልቅ ልምድን ይዞ በመመለስ በሰማያዊዎቹ ቤት ወደትልቅ ተጫዋችነት የሚያደርገውን ሽግግር በእጅጉ እያጠናከረ ይገኛል። 

ክርስቲንሰን በውሰት ሄዶ ስኬታማ ጊዜን አሳልፎ የመምጣቱ ነገርም ሌሎች ወጣቶች በስታምፎርድ ብሪጅ የዋናው ቡድን ተሰላፊነትን እድል የማግኘት ተስፋ እንደሚኖራቸው እንዲያስቡ መነሳሳት እንደሚፈጥርላቸው ተያይዞ ተገልጿል።

Advertisements