ቼልሲ ከ አርሰናል / የካራባኦ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ትንቅንቅ ቅድመ ዳሰሳ

ከዌስትብሮሚች ጋር በነበረው የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በዕለቱ የጨዋታው ዳኛ ማይክ ዲን በተሰጠባቸው ፍፁም ቅጣት ምት የተነሳ የዳኛውን ክብር በሚነካ ሁኔታ አርቢትሩን በማንቋሸሻቸው የሶስት ጨዋታ ቅጣት የተላለፈባቸው አርሰን ቬንገር ባሳለፍነው ሳምንት ከቼልሲ ጋር ያደረጉትንና በተመሳሳይ መልኩ በጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ ቡድናቸው በተሰጠበት የፍፁም ቅጣት ምት ነጥብ ጥሎ ለመውጣት የተገደደው ስብስባቸው ወሳኝ ተጫዋቾቹን በመነጠቅ እና በጉዳት እንዲሁም ደግሞ በውጤት ማሽቆልቆል እየታመሰ ዛሬ ምሽት በካራባኦ ካፕ ወይም በቀድሞ አጠራሩ በካርሊንግ ካፕ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ የአንቶኒዮ ኮንቴውን ቼልሲ ሜዳው ድረስ በማምራት ይገጥማል። እኛም ጨዋታን እንደሚከተለው ቅድመ ዳሰሳ አርገንበታል። 


“የጨዋታውን ዳኛ ውሳኔ በተመለከተ መጠየቅ እፈልጋለሁ። ምስሉን ብትመለከቱ ሀዛርድ እንዴት እንደወደቀና ፍፁም ቅጣት ምቱን እንዴት በፍጥነት እንደመታ ትመለከታላችሁ። ተጎድቶ ቢሆን ለምን ፍፁም ቅጣት ምቱን መታ? ሀዛርድን አልወቅስም። 

“እሱ ለቡድኑ ፍፁም ቅጣት ምት ለማስገኘት በጥሩ ሁኔታ ተንቃሳቅሷል።” በማለት ባሳለፍነው ሳምንት ረቡዕ ቡድናቸው ላይ በተሰጠው ቅጣት ምት ከቼልሲ ጋር አቻ ተለያይተው ነጥብ ለመጣል የተገደዱትበትን እና ባሳለፍነው አመት የካቲት ወር ላይ የአራት ጨዋታ እገዳ እንዲደርስባቸው ምክንያት የሆኗቸውን ዳኛ አንቶኒ ቴይለር ለመተቸት የተቻኮሉት ቬንገር አምና በሰማያዊዎቹ ቼልሲዎች 3 ለ 1 ሲረቱ እንደሆነው ሁሉ ዛሬም በቅጣት ጨዋታውን የሚመለከቱት በተለመደ ቦታቸው ላይ ሳይሆን ከደጋፊው ጋር በስታዲየሙ ምስራቅ አቅጣጫ መሆኑ ከወዲሁ ስጋት አሳድሮባቸዋል።

ፈረንሳዊው አለቃ ቡድናቸው ለከተማ ተቀናቃኙ እጅ ሲሰጥ ከአርሰናል ደጋፊዎች መቀመጫ በራቀና ወደመልበሻ ክፍሉ ለማምራት ብዙ በሚያስጉዘው የስታዲየሙ መቀመጫ ክፍል ሆነው የተመለከቱበትን ጨዋታ አንድ የማያውቁት ሰው ጭምር ሰላምታ ሰጥቷቸው “የአንተ አትክልተኛህ ነኝ” በማለት እየተናገረ ሲረብሻቸው እንደነበር አውስተው ሁኔታውን “በጣም ምቾት የሚነሳ” እና “ኋላቀር” ሲሉ ገልፀውታል። ዛሬ ምሽትም ያ እንዳይደገም ቀረብ ያለ ቦታ መርጠው ለመቀመጥ መዘጋጀታቸውን አያይዘው ተናግረዋል።

በዚህ ሁለቱ የለንደን ከተማ ተቀናቃኝ ክለቦች በአንድ ሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ በሚፋጠጡበት ትንቅንቅ ናቾ ሞኒሪያል፣ ሎረንት ኮሽሊ፣ ሰኢድ ኮሎንስሊያክ፣ አሮን ራምሴይ እና ኦሊቪ ዢሩን በጉዳት የማያገኙት ቬንገር ሜሶት ኦዚልን በጉዳት ሊሰልፍ እንደማይችል መነገሩ ትልቅ ጭንቀትን በአርሰናል ካምፕ የፈጠረ ሆኗል። ከዚህ ጋር በተያያዘም ፈረንሳዊው የመድፈኞቹ አለቃ ስብስባቸው ከመሳሳቱ የተነሳም ዛሬ ምሽት ወደ ማንችስተር ሲቲ ለማምራት ጫፍ እንደደረሰ የሚወራለትን አሌክሲ ሳንቼዝ ይዘው ወደሜዳ ለመግባት መገደዳቸው ተነግሯል።

በተያያዘ መረጃም ከሁሉም የቡድናቸው ስብስብ ክፍል በመከላከል ስፍራ ላይ ይበልጥ የተገደበ አማራጮች ያላቸው በመሆኑ ከግሪክ ያመጡትና ከቀናት በፊት በውሰት ለመስጠት እንደተዘጋጁ የተናገሩለትን የ 20 አመቱን የመሀል ተከላካይ ኮንስታንቲኖስ ማቭሮፓኖስን በተቀያሪ ስብስባቸው ለማከተት መወሰናቸው ታውቋል።

በሌላ በኩል ከባት ጉዳት አገግሞ በዛሬው ምሽት ጨዋታ ወደሜዳ እንደሚመለስ የተነገረለትን ወሳኝ ተጫዋቹን ኤደን ሀዛርድን ይዞ ጨዋታውን የሚጀምረው የአንቶኒዮ ኮንቴው ቼልሲ ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ በትልቁ እየተገዳደረው ያለውንና በሁለቱ ቡድኖች የእርስበርስ ግንኙነት በዘመነ ጆሴ ሞውሪንሆ የቼልሲ የንግስና ዘመን የነበረውን የበላይነት ያሳጣውን አርሰናል በሜዳው በሚያደርገው የምሽቱ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ በተቻለው አቅም ለማሸነፍና መዘጋጀቱን ቀድሞ ባሳበቀ መልኩ ባሳለፍነው ቅዳሜ ከኖርዊች ጋር በነበረው የኤፍኤ ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ወሳኝ ተጫዋቾቹን አሳርፎ ወደሜዳ መግባቱ ይታወሳል።  ከምሽቱ ጨዋታ በፊት የክለቡ ጣሊያናዊ አለቃ አንቶኒዮ ኮንቴ ያደረጉት ንግግርም ለዛሬው ጨዋታ ትልቅ ትኩረት መስጠታቸውን ማረጋገጫ ይሆነናል። 

ኮንቴ በመግለጫቸው “ይህ ጨዋታ ለእኛ ወሳኝ የግማሽ ፍፃሜና ዋንጫ ለማሸነፍ የምንችልበትን እድል የሚፈጥርልን ነው። ለዚህ ጨዋታ መድረሳችን የሚገባን ሲሆን ከአርሰናል ጋር የሚኖረን ጨዋታ ከባድ ነው። ነገርግን በሁኔታው ደስተኛ ልንሆን ይገባናል። ምክንያቱም ለግማሽ ፍፃሜ መብቃት ችለናል። ለፍፃሜው ለመድረስም የተቻለንን ጥረት እናደርጋለን።” በማለት ከዛሬው ጨዋታ ውጤት ይዘው ለመውጣት እና ቼልሲን ለሰባተኛ ጊዜ ለካራቦአ ዋንጫ ፍፃሜ ለማድረስ ከወዲሁ እንደጓጉ አሳይተዋል።

ማርቲን አትኪንሰን በሚመሩት እና ሁለቱ ቡድኖች ለ 194ኛ ጊዜ ከሚፋጠጡበት የምሽቱ ትንቅንቅ በፊት ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን ድረስ በሁሉም ውድድሮች ላይ ባላቸው የእርስበርስ ግንኙነት አርሰናል 74 ጨዋታዎችን በመርታት ቀዳሚ ቢሆንም አርሰን ቬንገር ከቼልሲ ጋር ያላቸው የጨዋታ ሪከርድ ጥሩ የሚባል አይደለም። ቬንገር መድፈኞቹን እየመሩ ወደሜዳ በገቡት 60 ጨዋታ ማሸነፍ የቻሉት 1/3ኛውን ወይም 22 ያህሉን ብቻ ሲሆን 21 ጨዋታ ተሸንፈው ቀሪውን 17 ጨዋታ በአቻ ውጤት ፈፅመዋል። 

ዛሬ ምሽትስ? ቬንገር በአርሰናል ቤት ከዋንጫ ስኬት እየራቁ ከመጡበት ያለፉት 14 አመታት ወዲህ በብቸኝነት ስኬታማ ከሆኑበት የኤፍኤ ዋንጫ ጭምር በጊዜ በተሰናበቱበት የዘንድሮው የውድድር ዘመን ከዛሬ ምሽቱን ጨዋታ የሚጠበቅባቸው ቡድናቸው ውጤት ይዞ እንዲወጣና ለፍፃሜ አንድ እግሩን እንዲያስገባ ማድረግ ይሆናል። 

በሌላ በኩል ግን ከዚህ ቀደም ቼልሲ በ1997 በተመሳሳይ የግማሽ ፍፃሜ የካርሊንግ ካፕ ዋንጫ ጨዋታ በሁለቱም ዙር አርሰናልን ማሸነፉንና እና በተመሳሳይ ሁኔታ ቡድናቸው በአመቱ በተመሳሳይ ውድድር መድፈኞቹን 5 ለ 0 መርታቱን የሚያሳይ አይረሴ ታሪክ እንዳለ የሚያውቁት የኮንቴ ስብስብ አባላት በሜዳቸው በቀላሉ ለአርሰናል እጅ እንደማይሰጡ ይታመናል። 

Advertisements