አርሰናል እና ቫሌንሺያ በፍራንሲስ ኮክለን ዝውውር ስምምነት ላይ ደረሱ

የአርሰናሉ የተከላካይ አማካይ ፍራንሲስ ኮክለን ከ አስር አመት በኋላ መድፈኞቹን ለቆ ወደ ስፔን ለማቅናት ሁለቱ ክለቦች ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ተጫዋቹ በአንድ ወቅት የአርሰናል የመሀል ሜዳ በሚገባ መምራት ችሎ የነበረ ሲሆን በአጨዋወቱ ለቢጫና ለቀይ ካርድ የተጋለጠ ስለነበር የሚተቹትም አይጠፉም።

በተለይም ከሳንቲ ካዞርላ ጋር ጥሩ ጥምረት ፈጥረው የነበረ ጊዜ በመድፈኞቹ ደጋፊዎች የሚረሳ አይደለም።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በዚህ አመት የመሰለፍን እድል ሳያገኝ በመቅረቱ በተጠባባቂ ወንበር ላይ መቀመጥ መደበኛ ስራው አድርጎት ቆይቷል።

የጃክ ዊልሼር ከጉዳት መመለስ ደግሞ ይበልጥኑ ተጫዋቹ በመሀል ሜዳ ላይ ያለው ፉክክር ያጦዘው በመሆኑ የኮክለን የመሰለፍ እድሉን አጥቦታል።

በዚህም መሰረት የእንግሊዞቹ ፓላስ እና ዌስትሀም እንዲሁም የስፔኑ ቫሌንሺያ የተጫዋቹ ፈላጊ በመሆን በተከፈተው የዝውውር መስኮት ላይ ፍላጎታቸውን አሳይተዋል።

ነገርግን ኮክለን ምርጫው ወደ ስፔን ማቅናት በመሆኑ ቫሌንሺያ እና አርሰናል በ 12 ሚሊየን ፓውንድ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ስካይ ስፓርት እና ቴሌግራፍ የመሳሰሉት ጋዜጦች አረጋግጠዋል።

ተጫዋቹም የህክምና ምርመራውን ካደረገ በኋላ በይፋ የቫሌንሺያ ተጫዋች መሆኑ ይፋ ይደረጋል።

በተመሳሳይ አሌክሲስ ሳንቼዝ እና ኦዚል እስካሁን ድረስ የውል ማራዘሚያ አለመፈረማቸው ተከትሎ ከዚህ ወር በኋላ ከክለቡ ጋር መቀጠላቸው አጠራጣሪ ሆኗል።

በተለይ ሳንቼዝ ማን ሲቲዎች ፈላጊዎቹ በመሆኑ ቢዘገይም ተጫዋቹን ማስፈረማቸው እንደማይቀር ይጠበቃል።

Advertisements