ውዝግብ / የሲቪያና ማንችስተር ዩናይትድ የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ የትኬት ጦርነት ተጋግሎ ቀጥሏል

በቻምፒዮንስ ሊጉ የ 16ቱ ቡድኖች ፍልሚያ ማንችስተር ዩናይትድ ከስፔኑ ሲቪያ ያገናኘው ጨዋታ ያስከተለው የትኬት ዋጋ ጦርነት ተጋግሎ ቀጥሏል። 

የሁለቱ ክለቦች አለመግባባት የተከሰተው የላሊጋው ክለብ በስታዲየሙ በሚደረገው ጨዋታ ላይ የእንግሊዙ ክለብ እንግዳ ደጋፊዎች ለሚቀመጡበት ቦታ ለእያንዳንዱ የ 100 ዩሮ (89 ፓውንድ) ዋጋ ከማውጣቱ ጋር በተያያዘ ሲሆን ሁኔታው የዩናይትድ ደጋፊዎችን ሲያስቆጣ ክለቡ በበኩሉ ዋጋው እንዲቀንስ ሲቪላን ለማሳመን ጣልቃ እንዲገባ አስገድዶታል። 

ሲቪላ የትኬት ዋጋውን እንዲቀንስ በዩናይትድ በኩል የተደረገው ጥረት ባለመሳካቱና ሲቪያ አሻፈረኝ በማለቱ የኦልትራፎርዱ ክለብ የስፔኑ አቻው የጠየቀውን ዋጋ በሜዳው ለሚደረገው ጨዋታ የእንግዳው የሲቪያ ደጋፊዎች እንዲከፍሉ ዋጋ ያወጣ ሲሆን ከእያንዳንዱ ትኬት ሽያጩ የሚያገኘውን 40 ዩሮም (35 ፓውንድ) ደጋፊዎች በመልሱ ጨዋታ ወደስፔን ሄደው ለሚከፍሉት ተጨማሪ 40 ዩሮ የትኬት ዋጋ ማካካሻ እንዲሆናቸው ለማድረግ አቅዷል። 

ዴይሊ ሜይልን ጠቅሶ ካልቺዮ መርካቶ እንደፃፈው ከሆነ ሲቪያ በመልሱ ጨዋታ ለዩናይትድ ደጋፊዎች እያንዳንዳቸው 100 ዩሮ የሚያወጡ 2,450 ትኬቶችን ያዘጋጀ ሲሆን ተጨማሪ 200 ትኬቶችን ደግሞ በ 150 ዩሮ እንደሚሸጥ አስታውቋል። 

በተያያዘ ሌላ መረጃም የውዝግቡ አነሳሽ የሆነው ስፔኑ ክለብ ዩናይትድ የትኬት ዋጋ ጭማሪ በማድረጉና ለእንግዳ ደጋፊዎች የአምስት በመቶ የስታዲየሙን ክፍል ክፍት ባለማድረጉ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበርን (UEFA) እንደሚያነጋግር እና በእንግሊዙ አቻው ላይ ስሞታውን ለእግር ኳስ ማህበሩ እንደሚያቀርብ ማረጋገጫ መስጠቱ ፍጥጫውን ይበልጥ አጋግሎታል።

ይህ የካቲት ወር አጋማሽ ላይ እንደሚደረግ የሚጠበቀውና ወደሩብ ፍፃሜው ለመግባት ትልቅ ትንቅንቅ እንደሚኖረው የሚታመነው ጨዋታ ከወዲሁ በትኬት ዋጋ መነሻነት ትልቅ አትኩሮትን መሳብ መጀመሩም አነጋጋሪ ሆኗል።

Advertisements