ድርድር / በፍራንሲስ ኮክለን የዝውውር ዋጋ ዙሪያ ከስምምነት ላይ መደረሱ ተገለፀ

ቫሌንሲያ ለአርሰናሉ አማካኝ ተጫዋች ፍራንሲስ ኮክለን ዝውውር 12 ሚሊዮን ፓውንድ ለመክፈል መስማማቱ ተገልጿል። 

የእንግሊዙ ታማኝ የስፖርት ዜና ተቋም የሆነው ስካይ ስፖርት እንዳወራው የ 26 አመቱ ተጫዋች የፕሪምየር ሊጉ ክለቦች ከሆኑት ዌስትሀም ዩናይትድ እና ክርስቲያል ፓላስ የቀረበለትን የዝውውር ጥያቄ አልቀበልም ካለ በኋላ ወደስፔን ለመሄድ መዘጋጀቱንና በዝውውር ዋጋው ላይም ከስምምነት ላይ መደረሱ ታውቋል።

ፈረንሳዊው የመሀል ሜዳ ተጫዋች ላለፋት አንድ አስርታት በመድፈኞቹ ቤት የቆየ ባለትልቅ ልምድ ተጫዋች ቢሆንም በዘንድሮው የውድድር ዘመን በዋናው ቡድን ያለው የተሰላፊነት መጠን እጅጉን ያሽቆለቆለ ሲሆን በሁሉም ውድድሮች ላይ በቋሚነት መሰለፍ የቻለውም በሰባት ጨዋታዎች ላይ ብቻ ነው። 

ቬንገር በኢምሬትስ ቆይታው ደስታ የራቀውንና በአብዛኛው ከቋሚ አሰላለፍ ውጪ የሆነውን ተጫዋች ቀጣይ የአርሰናል ቆይታ በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄም “ኮክለን ክለቡን ሊለቅ ይችላል። ነገርግን ከውሳኔ ላይ አልተደረሰም።” በማለት የአማካኙ ክለቡን መልቀቅ አይቀሬ እንደሆነ የሚጠቁም አስተያየትን ሰጥተዋል።  

ኮክለን ስታዴ ላቫሎይስ የተሰኘውን የሀገሩን ክለብ በመልቀቅ መድፈኞቹን የተቀላቀለው በ 2008 ክረምት ሲሆን በ 2014/15 የውድድር ዘመን በአርሰናል ዋና ቡድን ሰብሮ እስኪገባ ድረስም በሎሪየንት፣ ፍሬቡርግና ቻርልተን የውሰት ቆይታ ማድረጉ አይረሳም። 

በኢምሬትስ ሁለት የኤፍኤ ዋንጫዎችን ያነሳው ፈረንሳዊው መድፈኛ የጃክ ዊልሻየር ዳግም ማንሰራራት እንዲሁም ደግሞ ከአሮን ራምሴይ፣ ግራኔት ዣካ እና ሞሀመድ ኤልኒኒ የገጠመው የተሰላፊነት ፉክክር ውጪ ውጪውን እንዲያማትር እንዳደረገው በዘገባው ተያይዞ ተልጿል።

በሌላ ተያያዥ መረጃ ደግሞ አርሰናል በመጪው ሰኔ የውል ስምምነቱ ከሚጠናቀቀው እንግሊዛዊው የቡድኑ አማካኝ ዊልሻየር ጋር በቀጣዩ ሳምንት የውል ማራዘም ድርድር እንደሚጀምር ተነግሯል። 

ከዚህ በተቃራኒው አሌክሲስ ሳንቼዝ እና ኦዚል እስካሁን ድረስ የውል ማራዘሚያ አለመፈረማቸውን ተከትሎ ከዚህ ወር በኋላ ከክለቡ ጋር መቀጠላቸው አጠራጣሪ ሲሆን በተለይ ሳንቼዝ ወደአጥብቆ ፈላጊው ማንችስተር ሲቲ የማምራቱ ነገር እርግጥ ነው።

Advertisements