የተረጋገጠ / ባርሴሎና ኮሎምቢያዊውን ተከላካይ አስፈረመ

የስፔኑ ኃያል ክለብ ባርሴሎና ከብዙ ክለቦች ጋር ስሙ ሲያያዝ የከረመውን ኮሎምቢያዊ የመሃል ተከላካይ የግሉ ማድረጉን በይፋ አሳውቋል፡፡

የካታላኑ ክለብ ወጣቱን የመሃል ተከላካይ የሪ ሚናን ለማስፈረም 11.8 ሚልዮን ዩሮ ለብራዚሉ ፓልሜይራስ የከፈለ ሲሆን ለአምስት አመት ተኩል በክለቡ መቆየት የሚችልበትን ውል አስፈርሞታል፡፡

በሳምንቱ መጀመሪያ ፊልፕ ኮቲንሆን በከፍተኛ ዋጋ በማስፈረም የፊት መስመሩን ያጠናከረ ሲሆን አሁን ደግሞ የኋላ ክፍሉን በማጠናከር ላይ ትኩረቱን በማድረግ ጠንካራውን ኮሎምቢያዊ የቡድኑ አካል አድርጓል፡፡

በውል ስምምነቱ መሰረት የተጫዋቹን ውል አቋርጦ መውሰድ የሚፈልግ ክለብ 100 ሚልዮን ዩሮ ውል ማፍረሻ መክፈል የሚጠበቅበት ይሆናል፡፡

ተጫዋቹ በ 2016 የብራዚሉን ክለብ ከተቀላቀለ በኋላ 33 ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን በተቀላቀለበት አመትም ክለቡን ለሊግ ሻምፒዮንነት ማብቃት የቻለ ሲሆን ከቀድሞ ክለቡ ሳንታ ፊ ጋር በመሆን የኮፓ ሱዳሜሪካ (የላቲን አሜሪካ የዩሮፓ ሊግ አምሳያ) ዋንጫን ማንሳት ችሏል፡፡

የሊጉ መሪ ባርሴሎና አንጋፋውን አርጀንቲናዊ ሃቪየር ማሸራኖን ወደቻይናው ክለብ ሄቤይ ቻይና ፎርቹን ለመሸኘት መቃረቡን ተከትሎ ሚናን የርሱ ተተኪ ለማድረግ መወጠኑ ታውቋል፡፡

Advertisements