የቶተንሐሙ ሊቀመንበር በሃሪ ኬንና ዴሊ አሊ የዝውውር ጉዳይ ላይ የክለቡን አቋም ገለፁ


የቶተንሐም ሆትስፐሩ ሊቀመንበር ዳንኤል ሌቪ በክለቡ ወጣት ከዋክብት ሃሪ ኬንና ዴሊ አሊ ዝውውር ላይ የክለቡ ሃሳብ ምን እንደሆነ ያሳወቁበትን ንግግር አድርገዋል፡፡

ከሪያል ማድሪድ ጋር በተያያዘ ስሙ በስፋት እየተነሳ ያለውና በሎስብላንኮዎቹ ቤት የሚለብሰውን ማልያ ቁጥር እንደመረጠ ሁሉ የተነገረለት ሃሪ ኬንና ሌላኛው የሪያል ማድሪድና የፓሪስ ሴንት ጀርሜይን የዝውውር ኢላማ መሆኑ የተዘገበው ዴሊ አሊ ቶተንሐም ላለፉት አመታት ላሳየው ድንቅ ብቃትና የውጤት ጉዞ ተጠቃሽ ሚናን የተወጡ ሲሆን በዘንድሮው አመትም የፖቼቲኖ ስብስብ ዋነኛ ተዋናዮች ሆነው ቀጥለዋል፡፡

ይህን ተከትሎ በበርካታ ታላላቅ ክለቦች አይን የገቡት ሁለቱ ተጫዋቾች በተለይም በዘንድሮው የዝውውር መስኮት ስማቸው በተደጋጋሚ እየተጠራ መገኘቱ ያሳሰባቸው ቆፍጣናው የክለቡ አስተዳዳሪ ሌቪ ክለቡ ተጫዋቾቹን የሚለቅበት ምንም ምክንያት እንደሌለ አረጋግጠዋል፡፡

ሌቪ በንግግራቸው” ለደጋፊዎቻችን ማሳወቅ የምፈልገው ለክለባችን ይጠቅማሉ የምንላቸውን ተጫዋቾች በሙሉ ለማቆየት መቶ በመቶ እርግጠኞች መሆናችንን ነው ፤ አሰልጣኛችን ከፈለገም ቡድኑን ሊያጎለብቱ የሚችሉ ተጫዋቾችን ማምጣት የምንችል ቢሆንም በጥሩ የዝውውር መስኮት ግን ዝውውሮችን ለማድረግ አዳጋች ነው”ብለዋል፡፡

ያለፉት ሁለት አመታት የሊጉ ከፍተኛ አስቆጣሪ ኬን እሑድ በተካሄደው የኤፍ ኤ ዋንጫ ጨዋታ ሁለት ጎሎችን ካስቆጠረ በኋላ ስለቀጣይ ቆይታው ከጋዜጠኞች ለቀረበለት ጥያቄ “መሻሻልና ማደግን ነው የምፈልገው ፤ ዋንጫዎችን ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡ ክለቤ ደሞ ለዋንጫ ክብሮች እስከታገለ ድረስ እዚህ በመሆኔ ደስተኛ ነኝ” ሲል መናገሩ ይታወሳል፡፡

Advertisements