የእግርኳስ ፌዴሬሽኑ ምርጫ ትኩሳትና ድንገተኛው የፊፋ ደብዳቤ መዘዝ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትና የስራ አስፈፃሚዎቹን ለመምረጥ የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴዎቹን ዝርዝር  ይፋ ቢያደርግም ከፊፋ በተፃፈ ደብዳቤ በዕቅዱ መሰረት ምርጫውን ለማካሄድ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ምርጫው የሚደረግበትን ጊዜ ለሶስተኛ ጊዜ ለማራዘም ተገዷል። ውዝግብ ያልተለየው የምርጫ ሂደትም አሁንም መቋጫ የሚያገኝ አይመስልም። ተከታዩ ፅሁፍም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የተራዘመ የምርጫ ውዝግብ እና የፊፋ የከረረ ጣልቃ ገብነትን እንዲሁም የሌሎች ሃገራት ተመክሮን እንደሚከተለው ተመልክቷል።

የምርጫው መራዘም ምክኒያት

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጥር 5፣ 2010 ዓ.ም በአፋር ሰመራ ምርጫውን ለማካሄድ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን በይፋ ገልፆ ነበር። ይሁን እንጂ የዓለም አቀፉ የእግርኳስ አመራር (ፊፋ) ታህሳስ 30፣ 2010 ዓ.ም (በደብዳቤው ላይ ቀኑ 8 December 2018? ተብሎ በስህተት መገለፁን ልብ ይሏል) የፃፈው ድንገተኛ ደብዳቤ አምስት ቀናት ብቻ የቀሩትን የምርጫ ቀን ወደሌላ ቀን እንዲራዘም ጠቁሟል።

ፊፋ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የፃፈው ደብዳቤ

ፊፋ የምርጫው ቀን እንዲራዘም ያደረገው ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ኃላፊ አቶ አቶ ዘሪሁን መኮንን ታህሳስ 20፣ 2010 ዓ.ም ተፃፈልኝ ባለው የፊፋ የምርጫ ደንብ (አንቀፅ 3.4 (ሲ)፣ አንቀፅ 3.5፣ አንቀፅ 4.2 እና አንቀፅ 2.2) ጥሰት “ስጋት” ምክኒያት ጉዳዩን መርምሮ በቀረበለት ጥያቄ መሰረት ምርጫው ከቻን ውድድር በኋላ (ከጥር 27፣ 2010 ዓ.ም በኋላ) እንዲካሄድ ጠቁሟል። ምክኒያቱ ደግሞ በቻን ውድድር ምክኒያት ምርጫውን “የሚቆጣጠርና ሚታዘብ” አካል ለመላክ የማይችል በመሆኑና የአቶ መኮንን የፊፋ ምርጫ ደንብ ጥሰት “ስጋት” ጥያቄን ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነም ገልፅዋል።

በዚሁ መሰረት የእግርኳስ ፌዴሬሽኑ ረቡዕ ዕለት አስቸኳይ ስብሰባ ከደረገ በኋላ በፃፈው ማሳሰቢያ (ማሳሰቢያው የተፃፈበት ቀን እና ፊርማ ባይሰፍርበትም) “ለስፖርት መገናኛ ብዙኃን በሙሉ” በሚል ጥር 5 ሊካሄድ የነበረው የፕሬዝዳንት እና የስራ አስፈፃሚ ምርጫው መራዘሙን የሚገልፅ መልዕክት ያለው ደብዳቤ ልኳል። 

እግርኳስ ፌዴዴሬሽኑ ምርጫው የተራዘመበት ምክኒያት ብሎ የገለፀው የደብዳቤው ይዘት ሁለት ነው። በቁጥር አንድ ላይ የሰፈረው እና በ”ቻን ውድድር ምክኒያት” ተብሎ የተገለፀው ፊፋ ከፃፈው ደብዳቤ ይዘት ጋር ተመሳሳይ ሲሆን፣ በተራቁ ቁጥር ሁለት ላይ የተገለፀው ምክኒያት “ከምርጫው በኋላ ሊፈጠር የሚችለውን ችግር ለመቅረፍ እንዲቻል የምርጫውን ጊዜ ከጥር 27፣ 2010 ዓ.ም ቀን በኋላ” እንዲደረግ ከፊፋ መጠየቁ ተገልፅዋል። ከምርጫው በኋላ ይከሰታል ተብሎ የታሰበውን ግን ደብዳቤው አይገልፅም።

ከምርጫው በኋላ ምን ችግር ሊፈጠር ይችላል?

የምስራቅ አፍሪካ ሁኔታ እንደሚያሳየው ከሆነ ፊፋ በፌዴሬሽኖች እና መንግስታት ላይ ጣልቃ ለመግባት እጁ ረጅም ነው። ምክኒያቱ ደግሞ በቀጠናው ላይ ያለው ትልቅ የእግርኳስ ልማት ድጋፍ ነው።

ፊፋ ለአፍሪካ አባላት ፌዴሬሽኖች በዓመት 250,000 ዶላር ድጋፍ ያደርጋል። በተለይ ደግሞ በምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ላይ የሚያደረገው ድጋፍ ከዚህም ከፍ እንደሚል በፋይናንስ ድጋፍ ፕሮግራም ስም በ2015 ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሰጠው 750,000 ዶላር ማሳያ ነው።

ይህ ዓመታዊ የልማት የገንዘብ ድጋፍ ደግሞ በአብዛኞቹ ፌዴሬሽኖች ላይ የችግር መንስኤ እና የፌዴሬሽኖቹ አመራሮች በፌዴሬሽኑ አሰራር ላይ እጃቸውን እንዲያስገቡ እና ህጋዊ አሰራሮችን እንዲያዛቡም አለፍ ሲልም እጃቸውን ወደፓለቲካው ጣልቃ ገብነት ድረስ እንዲረዝም ያደርጋቸዋል።

ፊፋ መንግስታት በእግርኳስ ሂደቶች ላይ ጠልቃ በመግባታቸው ምክኒያት ከፍተኛ ቅጣት የሚያስከትሉ ጠንካራ ህጎች ስላሉት የመንግስት ባለስልጣናት በዚህ ጥብቅ ህግ የተገደቡ ናቸው ተብሎ ይተሰባል። ይሁን እንጂ በፌዴሬሽኖቹ ባለስልጣናት የፈረጠመ የገንዘብ አቅም ምክኒያት የመንግስት ባለስልጠናቱ እጅ የማይጠማዘዝበት ሁኔታ አይኖርም ተብሎም አታይታሰብም።

ፊፋ መንግስታት በእግርኳሱ ላይ ጠልቃ እንዳይገቡ የሚከላከል፣ ይህን ደንብ በሚተላለፉት ላይም ከዓለም አቀፍ ውድድሮቹ እስከመታገድ የሚደርስ ጥብቅ ህግ በማውጣት ለፌዴሬሽኖቹ ከለላ ይሰጣል። ይሁን እንጂ የቀድሙ ጊዜያት ነበራዊ ሁኔታዎች እንደሚያሳዩት አንዳንድ ሃገራት ይህን ደንብ ጥሰው በመገኘት ለከፍተኛ ቅጣት ተደርገዋል።

በዚሁ መሰረት ፊፋ ከምርጫ አስፈፃሚው ኃላፊ አቶ መኮንን በደረሰኝ የ”ስጋት” ደብዳቤ የዓለም አቀፉ እግርኳስ አመራር አራት የምርጫ ደንቦች መጣሳቸው እንዳሰጋው ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በፃፈው ደብዳቤ ገልፅዋል።

በአቶ መኮንን ጥቆማ መሰረት ፊፋ ተጥሰዋል ያላቸው አንቀፃች መሰረታዊ ይዘቶች ደግሞ ባምርጫው ሂደት ላይ የመንግስታዊ አካላት ጠልቃ ገብነት፣ የተጓደሉ የኮሚቴ አባላት አለመሟላት እና ለተከታታይ ሁለት ዓመታት የምርጫ ኮሚቴ ሆኖ መስራት ናቸው።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከደብዳቤው መድረስ ማግስት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባም የፊፋን የደንብ ጥሰት ስጋት ተመልክቶ የምርጫ ጊዜው ከቻን ውድድር በኋላ እንዲራዘም ወስኗል። ፌዴሬሽኑ ይህን ሳያደርግ ቀርቶ ቢሆን ኖሮ ፊፋ እንደስጋት የቀረቡለት የምርጫ ደንብ ጥሰቶችን መርምሮ ፌዴሬሽኑን ጥፋተኛ ሆኖ ካገኘው ብሄራዊ ቡድኑን ከአለም አቀፍ ውድድሮች እስከማገድ የሚደርስ ጠንካራ የቅጣት ውሳኔ ሊያስተላልፍ ይችል ነበር። የከዚህ ቀደም ተመክሮዎች ዳግሞ ፊፋ ለእንደዚህ ዓይነቶቹ የደንብ ጥሰቶች ሩሩህ ልብ እንደሌለው ነው።

የፊፋ የከዚህ ቀደም መሰል የደንብ ጥሰት እና የቅጣት ውሳኔዎች

የዓለም አቀፉ የእግርኳስ አመራር አካል ተወዳጁ እግርኳስ ያለጣልቃ ገብነት ነፃ ስፖርታዊ መንፈስ ኖሮት እንዲካሄድ የመንግስት ጣልቃ ገብነትን የሚፃረሩ ግልፅ አንቀፆችን በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ አስፍሯል። ይህን ተላልፈው በሚገኙ ሃገራት ላይ ደግሞ እርምጃዎችን በመውሰድ በኩል ርህራሄ እንደሌለው የበርካታ ሃገራት ጉዳይ ማሳያ ነው። ከዚህ ከማንግስት ጣልቃ ገብነት ጋር በተያያዘም በቅርብ ጊዜያት የፊፋ የቅጣት ፈላፃ ካረፈባቸው እና ከባድ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ሃገራትን መካከል የተወሰኑት የሚከተሉት ናቸው።

ስፔን

የዓለም አቀፈ የእግርኳስ አመራር አካል (ፊፋ) የስፔን መንግስት በእግርኳስ ፌዴሬሽኑ ምርጫ ላይ ጣልቃ ገብቷል ብሎ በማመኑ ጣልቃ ገብነቱ የማያቆም ከሆነ የስፔን ብሄራዊ ቡድንን ከሩሲያው የ2018 ዓለም ዋንጫ እንደሚያግድ ያስጠነቀቀው ባለፍው የፈረንጆቹ ዓመት 2017 ነበር።

ሱዳን

ፊፋ መንግስት በእግርኳስ ፌዴሬሽኑ ላይ እጁን አስገብቷል በሚል የምስራቅ አፍሪካዋን ሃገር ሱዳንን ከአለም አቀፍ ውድድሮች ያገደው ባለፈው ኃምሌ 2017 ነበር። በሀገሪቱ ላይ በተጠለው እገዳ ምክኒያትም የሩብ ፍፃሜው ማጣሪያው ለመድረስ ተቃርበው የነበሩት አል ሂላል፣ አል መሪክ እና አል ሂላል ኦቢየድ የተሰኙት የሃገሪቱ ክለቦች ከካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ውድድሮች ውጪ እንዲሆኑ ተደርገዋል።

ኢራን

የኢራን መንግስት ዳግመኛ የተመረጡትን የእግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት፣ አሊ ካፋሺያንን ከስራቸው እንዲለቁ ግፊት በማድረጉ የመካከለኛው ምስራቅ ሃገሯ ኢራን በፊፋ ከውቡ የዓለም አቀፍ የእግርኳስ ውድድር እንድትታገድ የሆነችው በ2017 ነበር።

ኩዌት

በመንግስት ጠልቃ ገብነት ምክኒያት እ.ኤ.አ. በ2007 እና 2008 ለሁለት ጊዜያት ያህል ከአለም አቀፍ ውድድሮች የታገደችው ኩዌት በእግርኳስ ፌዴሬሽኗ ላይ ጣልቃ እንድትገባ ምክኒያት ነው የተባለው ተፅዕኖ ፈጣሪው የስፖርቶች ወኪሉ ሼኽ አህመድ አል ፋህዳ አል-ሳባህ ህዳር 2017 ከዓለም አቀፍ ውድድሮች ታግዶባታል።

ሩሲያ 

ፊፋ የሩሲያ ዓለም ዋንጫ ዋና ኃላፊ እና የሩሲያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊ የሆኑት ቪታሊ ሙትኮ ከሩሲያው ጠቅላይ ሚኒስቴር ጋር ባላቸው ግንኙነት ምክኒያት የመንግስታዊ ጣልቃ ገብነት አላቸው ተብሎ በመታመኑ ከፊፋ የምክር ቤት አባልነታቸው እንዲነሱ የተደረገውም በ2017 ነበር።

ማሊ 

በ2015 የማሊ እግርኳስ ማህበር የመንግስት ጣልቃ ገብነት አለበት ብሎ በማመኑ ብሄራዊ ቡድኑ ከየትኛውም የዓለም አቀፍ ውድድሮች ለስምንት ሳምንታት ያህል በእግድ አቆይቷል።

ናይጄሪያ 

ናይጄሪያ የእግኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንቷ አሚኑ ሚያጋሪ ከ2014 የብራዚል ዓለም ዋንጫ ሲመለሱ ለእስር ቢዳርጋቸውም፣ ፊፋ ድርጊቱን የመንግስት ጠልቃ ገብነት ነው በሚል ሃገሪቱን ለዘጠኝ ቀናት ከዓለም አቀፍ ውድድሮች አግዶ በመቆየት ፕሬዝዳንቱ ወደቀድሞው ስልጣናቸው በመመለሳቸው ምክኒያት እግዱን አንስቷል።


ፔሩ

የዓለም አቀፉ የእግርኳስ አመራር አካል የፔሩ እግርኳስ ፌዴረሽን እ.ኤ.አ. በ2008 የመንግስት ጣልቃገብነት አለበት ብሎ በማመኑ ሃገሪቱን ከዓለም አቀፍ ውድድሮች አግዷል።

Advertisements