ሀሰተኛ / የማንችስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች በተሳሳተ የትዊተር መልዕክት ሲደሰቱና መልዕክቱን እርስበርስ ሲቀባበሉት አመሹ


የማንችስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች ፓውሎ ዲባላ ለክለባቸው እንደፈረመ የሚገልፅን የተሳሳተ የአዲዳስ የትዊተር ገፅ ላይ ወጣ የተባለን መልዕክት በማመን ሲፈነጥዙና መልዕክቱን በትዊተር ገፃቸው ሲቀባበሉ አምሽተዋል። 

ይህ በጀርመኑ ትጥቅ አምራች ድርጅት የትዊተር ገፅ እንደወጣ የተነገረለት መልዕክት የውሸት መሆኑንና በያዝነው የጥር የዝውውር መስኮት ክለባቸው አዲስ አጥቂ እንደሚያስፈርምላቸው ተስፋ ባደረጉት የቀያይ ሴይጣኖቹ ደጋፊዎች ዘንድ መገረምን ለመፍጠር የታሰበ መሆኑም ታውቋል።

የዛሬውን አይነት የውሸት የትዊተር መልእክት ከዚህ ቀደም ፊሊፕ ኩቲንሆ ወደባርሴሎና የሚያደርገውን ዝውውር ከማጠናቀቁ በፊት ዝውውሩን እንደጨረሰ ተደርጎ በሌላኛው የትጥቅ አምራች ተቋም ናይክ ስም መለቀቁ አይረሳም። 

የጀርመኑ ትጥቅ አምራች ኩባንያ ለአስር አመታት በሚቆይ ስምምነት በ 750 ሚሊዮን ፓውንድ የክብረ ወሰን ዋጋ የኦልትራፎርዱ ክለብ የመለያ ስፖንሰር ከሆነ ጥቂት አመታትን አስቆጥሯል።

Advertisements