ኤይቶር ካራንካ የቀድሞውን ታላቅ ክለብ ወደፕሪምየር ሊግ ለመመለስ ወደእንግሊዝ መጡ


ስፔናዊው የቀድሞው የሪያል ማድሪድ ምክትል አሰልጣኝ ኤይቶር ካራንካ በአንድ ወቅት የእንግሊዝ ሊግ ከሚገኙ ታላላቅ ክለቦች አንዱ የነበረውንና በአውሮፓ ጭምር መንገስ ችሎ የነበረውን ክለብ ወደፕሪምየር ሊጉ የመመለስ አላማን አንግበው ዳግም ወደእንግሊዝ እግር ኳስ ተመልሰዋል፡፡

በጆዜ ሞውሪንሆ የአስተዳደር ዘመን የፖርቱጋላዊው ምክትል በመሆን ሎስ ብላንኮዎቹን መምራት የቻሉት ካራንካ ከዚህ ቀደም በሊጉ ሲሳተፍ የነበረውን ሚድልስቦሮ እየመሩ በሊጉ ቆይታን ማድረግ ችለው የነበረ ሲሆን ከ 10 ወራት በፊትም ከዚህ ስራቸው መሰናበታቸው ይታወሳል፡፡

አሁን በእንግሊዝ ሁለተኛ ዲቪዚዮን የሚጫወተውን ኖቲንግሃም ፎረስትን ወደሊጉ እንደሚመልሱ የታመነባቸው አሰልጣኙ በሳምንቱ መጀመሪያ ከክለቡ ጋር ውል ከፈፀሙ በኋላ የቀድሞውን ዝነኛ ክለብ ወደክብሩ ለመመለስ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

የ 44 አመቱ ካራንካ ሲናገሩ “የክለቡ ባለቤቶችና እኔ ተመሳሳይ የሆነ ኢላማ አለን ፤ ይህም ኖቲንግሃም ፎረስትን ወደትልቁ ሊግ ማምጣት ነው፡፡በሁለት አመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ክለቡን ወደሊጉ የመመለስ ዕቅድን ይዣለሁ፡፡በዚህ አመት ወይም በቀጣዩ አመት ይህን ካሳካን እሰየው ነው፡፡ ካልሆነም ደጋፊዎችን የምመክረው ተረጋግተው እንዲጠብቁ ነው ” ብለዋል፡፡

ፎረስት በሻምፒዮንሺፑ 14ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ወደሊጉ ለማለፍ የሚደረገውን ጥሎማለፍ ማካሄድ ከሚያስችለው የስድስተኝነት ደረጃ በ 11 ነጥብ ዝቅ ብሎ ይገኛል፡፡

Advertisements