የህይወት ተገላቢጦሽ / የትናንት ቢሊየነር የዛሬ የአዕምሮ ታማሚው ናይጄሪያዊ ኮከብ!

የትናንት ቅጥ ያጣ ህይወታቸው ከራሳቸው አልፎ ለሀገራቸው የተረፉ፣ነገርግን ከጊዜ ኡደት ጋር ሀብታቸውን ሳይጠብቁ ዛሬ ላይ ለችግር ተጋልጠው ኑሯቸውን በጎዳና ያደረጉ፣ማንነታቸውን ዘንግተው እራሳቸውን የረሱ የአፍሪካ ኮከቦች አሁንም በየቦታው አሉ።

በቅርቡ በአርሰናል ደጋፊዎች ይወደድ የነበረው ሀብትን ከጫፍ እስከ ጫፍ የተመለከተው አይቮሪኮስታዊው ኢማኑኤል ኤቡዬ የደረሰበትን አሳዛኝ የህይወት ተገላቢጦሽ የአለም መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

ኢቡዬ ለአመታት እየሰራ ለባለቤቱ ሲልከው የነበረው ረብጣ ሚሊየን ፖውንዶች ተወርሶበት ከዘመናዊ መኪና ወደ ህዝብ የጋራ መገልገያ ትራንስፖርት፣ከቅንጡ መኖሪያ ቤት ወደ ሰው በረንዳ ያሽቆለቆለበትን አሳዛኝ የህይወት ውጣ ውረድ የብዝዎቹን ልብ ነክቶ አልፏል።

አሁን ደግሞ ናይጄሪያዊው የቀድሞ ኮከብ ተጫዋች የሆነው ዊልሰን ኦሩማ በአዕምሮ ህመም እየተሰቃየ እንደሆነ ከወደ ናይጄሪያ የወጡ መረጃዎች አመላክተዋል።

በፈረንሳይ እና በግሪክ ክለቦች ሰፋ ያለ ቆይታ የነበረው የቀድሞው ኮከብ ለፈረንሳዩ ማርሴ፣ሌንስ፣ናንሲ፣ኒምስ እንዲሁም ለግሪኩ ካቫላ መጫወት ችሏል።

2010 ላይ በ 33 አመቱ ከእግርኳስ አለም ጫማውን ሰቅሎ ጡረታ እስኪወጣ ድረስ በተለያዩ ክለቦች ያገኘውን ወደ ሀገሩ የመገበያያ ገንዘብ [ናይራ] ሲቀየር በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘቡ ዛሬ አብሮት የለም።

ኦሩማ 2012 ላይ ስሙ ባልታወቀ ፓስተር ተታሎ በፀፀትና በብስጭት ቀድሞ ይታወቅበት ከነበረው ቅንጡ ህይወቱ በተገላቢጦሽ ጤናው ተጓድሎ በአዕምሮ ህመም እየተሰቃየ ይገኛል።

ያልታወቀው ፓስተር(ካህን) ከስድስት አመት በፊት ጫን ያለ የገንዘብ ሀብት ወደነበረው ዊልሰን ኦሩማ ጋር በመቅረብ በነዳጅ ቢዝነስ ላይ እንደሚሰራ ከበርቴ መስሎ ግንኙነት መፍጠር ጀምሯል።

የቀድሞ ኮከቡ ዊልሰን ኦሩማ ወደ ቢዝነሱ ቢገባ እንደሚያዋጣው እያስረዳ የራሱን ተሞክሮ የሀሰተኛ ማስረጃዎች በማቅረብ እውነት ለማስመሰል ይጥራል።

ሀሰተኛ ማስረጃዎቹን ለመለየት ያልቻለው ኦሩማ ፓስተሩን በማመን ወደ ቢዝነሱ ለመግባት የተጠየቀውን ገንዘብ በድምር 1.2 ቢሊየን ናይራ ይሰጠዋል።

ኦሩማ በፈረንሳዩ ኦሎምፒክ ደ ማርሴ መጫወት ችሏል።

ድራማውን በሚገባ የሰራው ፓስተሩ ገንዘቡን ከተቀበለ በኋላ ተመልሶ ዊልሰን ኦሩማን ማግኘት ሳያስፈልገው ዱካውን አጥፍቷል።

ናይጄሪያዊው የቀድሞ ኮከብ ዛሬ ላይ እራሱን ጥሎ የአዕምሮ ህመምተኛ ለመሆን ያበቃውን ከባድ ስህተት የፈፀመው ለፓስተሩ የተጠየቀውን ቢሊየን ናይራ አሳልፎ በመስጠት የተታለለበት ጊዜ እንደሆነ የቅርብ ወዳጆቹ ተናግረዋል።

ኢማክፖር ዲቦፈን የተባለ የቅርብ ጓደኛው የቀድሞው ኮከብ አሁንም ድረስ ካጋጠመው የአዕምሮ ህመም እንዳላገገመ ተናግሯል።

“ዊልሰን ኦሩማ ከተታለለ በኋላ ያጋጠመው የአዕምሮ ህመን እስካሁን ማገገም አልቻለም።ህክምና ለማድግ የተለያዩ ቦታዎች ሄዷል፣ነገርግን ከትንሽ መሻሻሎች በኋላ ችግሩ እየከፋ ሄዷል።” ሲል ስለ ጓደኛው ጤንነት ተናግሯል።

የቀድሞ የቡድን አጋሮቹ ኦሩማን ለመርዳት የገንዘብ ማሰባሰቢያ ጨዋታ ሊያደርጉ እንደሆነ ተሰምቷል።አብረውት ከተጫወቱት ውስጥ ንዋንኮ ካኑ፣ሳምሶን ሲያሲያ፣ኢጉቮኦን እና አካኒ በእለቱ ከሚጫወቱት ውስጥ እንደሚገኙ ታውቋል።

ጨዋታውም በናይጄሪያ ሌጎስ በወርሀ የካቲት ላይ እንዲደረግ ለማድረግ እንደታሰበ ተነግሯል።

ዊልሰን ኦሩማ በድንቁ የ 1996 የናይጄሪያ የኦሎምፒክ ቡድን አባል ነበር

ከቀድሞ ናይጄሪያዊያን ሌሎች ኮከቦች ጄጄ ኦካቻ እና ንዋንኮ ካኑ ጋር መጫወት የቻለው ኦሩማ በአስደናቂው የ 1996ቱ የናይጄሪያ የኦሎምፒክ ቡድን ውስጥ ተካቶ የዋንጫ አሸናፊ መሆን ችሏል።

በ 2002 እና በ 2006 የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ናይጄሪያ የነሀስ ሜዳሊያ ስታሸነፍ የቡድኑ አባል በመሆን መጫወት ችሏል።

በወጣትነቱ እንዲሁ ለናይጄሪያ ከ 17 አመት በታች በመሰለፍ በ 1993 የፊፋ ከ 17 አመት በታች የአለም ዋንጫ አሸናፊ ነበር።


Advertisements