የዕለተ አርብ የአውሮፓ ጋዜጦች አጫጭር ዝውውር ወሬዎች 

የአውሮፓ የጥር ወር የዝውውር መስኮት አሁንም ተጧጥፎ እንደቀጠለ ይገኛል። ኢትዮአዲስ ስፖርትም በዛሬው ዕለት በአውሮፓ ጋዜጦች ትኩረትን የሳቡ አበይት የዝውውር ርዕሰ ጉዳይ ናቸው ያለቻቸውን ወሬዎችን እንደሚከተለው አሰናድታለች።

እንግሊዝ

ማን ዩናይትድ ዊግልን ለማስፈረም የሚደረገውን ፉክክር በቀዳሚነት እየመራ ነው

ማንችስተር ዩናይትድ የቦሩሲያ ዶርትሙንዱን አማካኝ ኹሊየን ዊግልን ለማስፈረም የሚደረገውን ፉክክር ከማንችስተር ሲቲ ቀድሞ እየመራ እንደሚገኝ የዘ ኢንዲፔንደንት ጋዜጣ ዘገባ አመልክቷል።

ጆዜ ሞሪንሆ ፓል ፖግባን የሚያግዝ የተከላካይ አማካኝ ተጫዋች የሚፈልጉ በመሆናቸው በሲቲ ጭምር የሚፈለገውን ዊግልን በቀያይ ሰይጣኖቹ የዝውውር ዒላማ ውስጥ ማስገባታቸውን ተናግረዋል።

በዝውውሩ ሄነሪክ ሚክሂታሪያንን የቅያሪ አካል ማድረጉ የማይሳካ ቢመስልም ዩናይትድ ግን የዊግልን ዝውውር ለማቀላጠፍ እንዲችል አማካኝ ተጫዋቹን ወደዶርትሙንድ ለመላክ ፈቃደኛ ነው።


ማህሬዝ ከሊቨርፑል ጋር ንግግር ጀምሯል

እንደኤክስፕሬስ ጋዜጣ ዘገባ ከሆነ የሌስተሩ የክንፍ ተጫዋች ሪያድ ማህሬዝ በጥር ወር መዛወር በሚቻልበት የስምምነት ጉዳይ ከሊቨርፑል ጋር ንግግር ጀምሯል።

ቀዮቹ ፊሊፔ ኮቲንሆን ለባርሴሎና ከሸጡ በኋላ ሁነኛ ምትክ የሚሆናቸውን ተጫዋች ለማግኘት ገበያውን እየተመልከቱ የሚገኝ ሲሆን አልጄሪያዊ ተጫዋች ደግሞ ጥሩ አማራጭ ሆኖ አግኝተውታል።

ማህሬዝ ምንም እንኳ ስስካሁን ምንም አይነት ግንኙትነት ባይኖረውም ወደአርሰናል መዛወር ፍለጎት ያለው ቢሆንም ለየርገን ክሎፕ ለመጫወት ዝግጁ መሆኑ ግን ተገልፅዋል።

ኤቨርተን ዋልኮትን ማስፈረም ፈልጓል

የኤቨርተኑ አሰልጣኝ ሳም አላርዳይስ ክለባቸው በዚህ ወር የአርሰናሉን የክንፍ ተጫዋች፣ ቲዮ ዋልኮትን ማስፈረም እንደሚፈልግ ገልፅዋል።

“ሁላችሁም በቲዮ ላይ ያለንን ፍላጎት ታውቃላችሁ።” ሲሉ አላርዳይስ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ ገልፀው “ያንንም ወደመስመር ማስገባት የምንችል ከሆነ ደስተኛ እሆናለሁ።” ሲሉ ገልፀዋል።

ማን ዩናይትድ ቫርዲን እና ኻቪየር “ቺቻሪቶን” ለማስፈረም አስቧል

ማንችስተር ዩናይትድ 35 ሚ.ፓ ዋጋ ያለውን ጄሚ ቫርዲን እና 17 ሚ.ፓ ዋጋ ያለውን የቀድሞ ተጫዋቹን ኻቪየር “ቺቻሪቶ” ኸርናንዴዝን ከአሌክሲ ሳንቼዝ በተጨማሪ የዝውውር ዒለማቸው ውስጥ አስገብተዋል።

አሌግሪና ኢነሪኬ በቼልሲ የዝውውር ዒለማ ውስጥ ገብተዋል

እንደደይሊ ሜል ዘገባ ከሆነ ቼልሲ አንቶኒዮ ኮንቴ በውድድር ዘመኑ መጨረሻ ክለቡን የሚለቁ ከሆኑ ማሲሚላኖ አሌግሪን እና ልዊስ ኢነሪኬን በአሰልጣኝነት ለመሾም አቅዷል።

ስፔን

ሪያል ማድሪድ ኔይማርን የሚያገኝበት አማራጭ እንዳለው አምኗል

ሪያል ማድሪድ ትልቅ ስም ያለው “ጋላክቲኮ” ተጫዋቾችን የማስፈረም ፍላጎት ያለው ሲሆን፣ ከአበይት ዝርዝሮቹ ውስጥም ኔይማርን አካቷል። ሎስ ብላንኮዎቹ የፒኤስጂውን የፊት ተጫዋች ማስፈረም ውስብስብ ጉዳይ እንደሚሆንና እስከ2019 ክረምት ድረስ ተጫዋቹን ማዛወር ሊሆን የማይችል እንደሆነ ያውቃሉ። ነገር ግን ተጫዋቹ እነሱን የመቀላቀል ከፍ ያለ ፍላጎት እንዳለውና በአንፃሩ ፒኤስጂ ክርስቲያኖን እንደሚፈልግ ያምናሉ። ይህ ደግሞ ስምምነቱን ቀላል የሚያደግላቸው ነገር ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ስምምነቱ የማይሆን ከሆነ ሃሪ ኬንን፣ ኤዲን ሃዛርድን እና ቲሞ ዋርነርን የማስፈረምን ጉዳይን ሊያጤኑበት እንደሚችሉ የማርካ ዘገባ አመልክቷል።

መሱት ኦዚል ወደባርሴሎና የመዛወር ፍላጎት አለው

እንደ ሙንዶ ዲፖርቲቮ ጋዜጣ ዘገባ ከሆነ መሱት ኦዚል በጥር ወር ወደባርሴሎና የመዛወር ከፍተኛ ፍላጎር ያለው ቢሆንም፣ የካታሎኑ ክለብ ግን በክረምቱ በነፃ ሊያገነው ለሚችለው ተጫዋች የዝውውር ወጪ ለማውጣት ፈቃደኛ አይደለም። ይልቁኑ የመጀመሪያ ምርጫቸው በሆነው ፊሊፔ ኮቲንሆ ላይ ማርጋት ምርጫውን አድርጓል። 

ቬንገር ሳንቼዝ አርሰናልን እንደማይለቅ አሳውቀዋል

አርሰን ቬንገር በሁለቱ የማንችስተር ከተማ ክለቦች መካከል በአሌክሲ ሳንቼዝ ላይ ምንም አይነት የዝውውር ጥያቄ ጦርነት እንደሌለ ተናግረዋል።

ፈረንሳዊው አሰልጠኝ ስለቺሊያዊው ተጫዋች የወደፊት ዕጣ ፈንታ ቃል ባይተነፍሱም የዝውውር ጥያቄዎች መኖራቸውን ግን አልካዱም።

ጉዌታ ወደክሪስታል ፓላስ ሊያመራ ይችላል

ቪሴንቴ ጉዌታ በ3.5 ሚ.ፓውንድ በሆነ ዋጋ ክለቡን እንዲለቅ በሚያስችለው ሁኔታ ከጌታፌው ኃላፊ ኤንጀል ቶሬሥ ጋር ስምምነት በማድረጉ በቀጣዮቹ ቀናት ወደክሪስታል ፓላስ ሊያመራ ይችላል። ፓላሶችም ይህንኑ የዝውውር ዋጋ ማቅረባቸውን ያመለከተው የማርካ ጋዜጣ ዘገባ ነው።

ሪያል ቤቲስ ሶስት ተጫዋቾችን ለማዛወር አቅዷል

ሪያል ቤቲስ ያለበትን የግራ መስመር የተከላካይ ስፍራ ክፍተት ለመድፈን ሲል ፓትሪስ ኤቭራ፣ ሚጉዌል ላዩንን እና ዳቪድ ሳንቶንን ለማስፈረም እያጤነበት እንደሚገኙ የክለቡ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ሎሬንዞ ሴራ ፌሬራ መግለፃቸውን ስታዲዮ ዴፖርቲቮ ዘግቧል።

ፈረንሳይ

ሴሪ የማንችስተር ሲቲ የዝውውር ዒላማ ውስጥ ገብቷል

እንደለ ፓሪሲያን ጋዜጣ ዘገባ ከሆነ ዣን-ሚካኤል ሴሪ የማንችስተር ሲቲ የዝውውር ዒላማ ውስጥ ገብቷል። ፔፕ ጋርዲዮላ በአራት ውድድሮች ላይ ያላቸውን ፉክክር ለማጠባናከር ሲሉ የኒሱን አማካኝ ፈልገዋል። ይሁን እንጂ ከአል-ጃዚራ ለማስፈረም ሲመለከቱት የነበረውን ላሳና ዲያራ ምትክ ይሆናቸው ዘንድ እያጤኑበት ከሚገኙት ፒኤስጂዎች ቀላል ፉክክር አይጠብቃቸውም። 

ንዶንግ በዋትፎርድ የሚፈለግ ተጫዋች ሆኗል

የሰንደርላንዱ አማካኝ ዲዲየ ንዶንግ የዋትፎርድ የዝውውር ዒላማ ውስጥ የገባ ተጫዋች መሆኑን የለ’ኪፕ ጋዜጣ ዘገባ አመልክቷል። የለንደኑ ክለብ 8 ሚ.ፓ በሆነ ዋጋ በቋሚነት ማስፈረም የሚያስችል አማራጭ ይዞ የ23 ዓመቱን ቷዋች በውሰት ለማዛወር አስቧል።

ጀርመን

የሆፈኒየሙ አማካኝ አሚሪ የቡንደስሊጋውን ክለብ ሊለቅ ይችላል

እንደስፖርት ቢልድ ዘገባ ከሆነ የሆፈኒየሙ አማካኝ ናዲም አሚሪ 15 ሚ.ፓ በሆነው ዝቅተኛ የውል ማፍረሻ ስምምነቱ ምክኒያት በክረምቱ የቡንደስሊጋውን ክለብ ሊለቅ የሚችልበት ዕድል አለ። የ21 ዓመቱ ተጫዋች ለዓመታት በሚፈለገው የማውሪሲዮ ፓቸቲኖው፣ ቶተንሃም የዝውውር ዒላማ ውስጥ የገባ ተጫዋች ነው። ነገር ግን ተጫዋቹ የኦዚል ምትክ ይሆናቸው ዘንድ በአርሰናልም የሚፈልግ ሲሆን፣ ማንችስተር ዩናይትድም ሌላው ፈላጊ ክለብ ነው።

ጣሊያን

የሪያል ማድሪድ የዝውውር ዒላማ የሆነው ኢካርዲ በዝውውር ዘመኑ መጨረሻ ኢንተርን ሊለቅ ይችላል

የሪያል ማድሪድ የዝውውር ዒላማ የሆነው ማውሮ ኢካርዲ ኢንተር ሚላን ለሻምፒዮንስ ሊጉ የማይበቃ ከሆነ በውድድር ዘመኑ መጨረሻ የጣሊያኑን ክለብ እንደሚለቅ ጋዜጣ ዴሎ ስፖርት ዘግቧል። 

አርጄንቲናዊው ተጫዋች መሰለፍ በቻለባቸው 176 የሴሪ ኣ ጨዋታዎች ላይ 99 ግቦችን ከመረብ ማሳረፍ ቢችልም እስከሁን ለክለቡ በሻምፒዮንስ ሊጉ ውድድር ላይ መሰለፍ ባለመቻሉ በክለቡ ላይ ያለው ትዕግስት ተሟጧል። 

የናፖሊው አሰልጣኝ ሳኔን ለማስፈረም ጥያቄ አቅርበዋል

የናፖሊው አሰልጣኝ ማውሪዚዮ ሳሪ ክለባቸው የማንችስተር ሲቲውን የክንፍ ተጫዋች ሊሮይ ሳኔን ለማስፈረም ጥያቄ ማቅረባቸውን ካልቾናፖሊ24 ዘግቧል።

ሪያል ማድሪድ የጀርመኑን ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኙን፣ ሎውን በአሠልጠኝነት ሊሾም ይችላል


እንደላ ስታምፓ ጋዜጣ ዘገባ ከሆነ ሪያል ማድሪድ በሻምፒዮንስ ሊጉ በፒኤስጂ ሽንፈት የሚደርስበት ከሆነ የጀርመን ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የሆኑትን ዮሃኪም ሎውን የመጀመሪያ አማራጩ አድርጎ በዒላማው ውስጥ ያስገባቸው በመሆኑ ዚነዲን ዚዳንን ሊያሰናብት ይችላል።

ጁቬንቱስ ቻንን ብቻ ሳይሆን የፔሌግሪኒም ፈላጊ ሆኗል

ጁቬንቱስ ለማስፈረም የሚፈልገው የሊቨርፑሉን አማካኝ ኤምሬ ቻንን ብቻ ሳይሆን በቼልሲ፣ ማንችስተር ሲቲ እና ማንችስተር ዩናይትድ ጭምር የሚፈለገውን የሮማውን ሎሬንዞ ፔሌግሪኒንም በዝውውር ዒላማው ውስጥ ያስገባው ተጫዋች ሆኗል። የ21 ዓመቱ ተጫዋች የውል ማፍረሻ ዋጋ 22 ሚ.ፓውንድ እንደሆነ ያመለከተው ቱቶ ስፖርት ዘገባ ነው።

ኢንተር ሎፔዝን በውሰት ለመውሰድ ፈልጓል

ኢንተር የቤኔፊካውን ተከላከይ ሊሰንድሮ ሎፔዝን በውድድር ዘመኑ መጨረሻ በ9.8 ሚ.ፓውንድ ማስፈረም በሚያስችል አማራጭ ስምምነት በውሰት ለማስፈረም መዘጋጀቱን ጋዜጣ ዴሎ ስፖርት ዘግቧል።

ፖርቱጋል

ስፖርቲግ ሊዝቦን ምንም እንኳ የቀድሞው የፓርቶ የፊት ተጫዋች ጃክሰን ማርቲኔዝ ለዝውውር የቀረበለት ቢሆንም ተጫዋቹን ከቻይናው ክለብ፣ ጉዋንዡ ኤቨርግራንዴ ላለማዛወር ውሳኔ ላይ መድረሱን ቦላ ጋዜጣ ዘግቧል።

Advertisements