ትእግስት አልባው በምክንያት የታጠረው የዛማሌኩ ሊቀመንበር ሞርታዳ ማንሱር አመራር

6

ስማቸው ለመላው አፍሪካ እንግዳ አይደለም፡፡በተለይ በሰሜናዊቷ አፍሪካ ከ1990ዎቹ መጀመሪያ በኋላ እሳቸውን የማያውቅ ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡በሙያቸው የህግ አማካሪ ቢሆንም በሚሰጧቸው አወዛጋቢ መግለጫዎች ይታወቃሉ፡፡እኝህ ሰው የወቅቱ የግብጹ ዛማሌክ ሊቀመንበር የ 65 አመቱ ሞርታዳ አህመድ ሞሀመድ ማንሱር ናቸው፡፡የኢትዮአዲስ ስፖርት ጸሀፊው ዕዮብ ዳዲም ስለአወዛጋቢው ሊቀመንበር ቀጣዩን ጹሁፍ አዘጋጅቷል፡፤

ተጽእኖ ፈጣሪነታቸው በክለብ ብቻ እንዲወሰን ፍላጎት አልነበራቸውም፡፡ይህንን ሀሳባቸውን በማጠናከር አገራቸው ግብጽን ለመምራት እቅዱ ነበራቸው፡፡2014 ላይ ለሶስተኛ ጊዜ የዛማሌክ ክለብ ፕሬዝዳንት ሆነው ከተመረጡ በኋላ ቀጣዩ የቤት ስራቸውን ለግብጽ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ መወዳደር እንደሆነ አሳወቁ፡፡ፍላጎታቸውንም በይፋ ገልጸው ቅስቀሳቸውን ጀመሩ፡፡

በወቅቱ ሞርታዳ ማንሱር ገና ከጅምሩ 20ሺ የሚያህል የድጋፍ ድምጽ በትነውት ከነበረው የድጋፍ ቅጽ ላይ ማረጋገጫ አግኝነው ስኬታማ እንደሚሆኑ ተስፈኛ ቢሆኑም ከቀድሞው የመከለካያ አለቃ አብድል ፈታህ ኤል ሲሲ እንዲሁም ከግራ ዘመሙ ፖለቲከኛ ሀምደን ሰባሂ ጋር ብርቱ ፉክክር እንደሚጠብቃቸው ግን አልዘነጉትም፡፡

ነገርግን እኚህ አወዛጋቢ ሰው እጩ ተወዳዳሪ ሆነው እንደሚቀርቡ ካሳወቁ ከጥቂት ቀናት በኋላ እራሳቸው ከፕሬዝዳንታዊ የምርጫ ውድድር ማንሳታቸው በማሳወቅ ደጋፊዎቻቸውን አስደነገጡ፡፡አስገራሚው ነገር እሳቸው ከፖለቲካ ጡዘቱ በጊዜ እጃቸውን መስጠታቸው ሳይሆን ከፉክክሩ የወጡበት ምክንያት ነበር፡፡

ፈጣሪ መልእክት ልኮልኛል፡፡ምልክትም ሰጥቶኛል፣አሸናፊ የሚሆነው የመከለካያ አለቃው አብድል ፈታህ ኤልሲሲ ነው፡፡ስለዚህ ከፉክክሩ እራሴን አግልያለው፡፡” በማለት አስገራሚ ንግግር ተናገሩ፡፡

መጋቢት 2014 ላይ ተፎካካሪያቸውን ከማል ዳርዊሽን አሸንፈው በድጋሚ የዛማሌክ ሊቀመንበር ሆነው ሲመረጡ በማህበራዊ ሚዲያዎች ጥቂት ማይባሉ የክለቡ ደጋፊዎች ምርጫውን ተቃውመውታል፡፡በተለይ የክለቡ ጽንፈኛ ደጋፊዎች የሳቸውን ያለፉት ስህተቶችን እየነቀሱ የክለቡን ስኬት እንዳያቀጭጩት ስጋት ነበራቸው፡፡

ሰውየው ሀላፊነታቸው ላይ ከወጡ በኋላ ዛማሌክ ማሸነፍ ባልቻለ ቁጥር ወይንም ባላንጣቸው አል አህሊ ሲበረታ የተለያዩ ምክንያቶችን ማቅረብ እና ቡድናቸው ከሊጉ ውድድር እንደሚወጣ መዛት መለያቸው ሆኗል፡፡

በመጋቢት 2017 ላይ ዛማሌክ በአልማቃሳ 1-0 ከተሸነፉ በኋላ ጨዋታው ካልተደገመ ውድድሩን ለማቋረጥ እንደሚገደዱ አሳውቀው ነበር፡፡በጨዋታው ዛማሌኮች የፍጹም ቅጣት ምት ጥያቄ ቢያቀርቡም ዳኛው ጨዋታውን አስቀጥሏል፡፡በዚህም የተበሳጩት ዛማሌኮች ከጨዋታው በኋላ በሊቀመንበራቸው አማካኝነት ለሽንፈታቸው ዳኛውን ተጠያቂ አደረጉ፡፡

7.jpg

የአልማቃሳ ጨዋታ ካልተደገመ እራሳችንን ከግብጽ ፕሪምየር ሊግ እናገላለን፡፡በመቀጠልም በአረብ ውድድሮች እና በቻምፕየንስ ሊጉ ላይ ብቻ ተሳታፊ እንሆናለን፡፡”ሲሉ ጠንካራ መግለጫ በማቅረብ ዳኛውን ወነጀሉ፡፡

ሞርታዳ ማንሱር ይህንን ጨዋታ ቀደም ብለው ለማቋረጥ አስበው እንደነበረም አልሸሸጉም

ጨዋታውን ለማቋረጥ አስበን የነበረው ዳኛው እንደተሳሳተ ነበር፡፡ ነገርግን የክለባችን ምክትል ፕሬዝዳንት ተጫዋቾቹ ከ15 ደቂቃ በኋላ ሜዳውን እንዲለቁ ቀደም ብሎ ነግሯቸው ነበር፡፡ ነገርግን ጨዋታው ከመጠናቀቁ ሶስት ደቂቃ ቀደም ብሎ ቡድኑ ሜዳውን ቢለቅ ትርጉም ስለሌለው እንዲቀጥሉ ተደርገዋል፡፡”በማለት ለአንድ ግብጽ ቴሌቭዥን ሀሳባቸውን በምሬት በመግለጽ ቅሬታቸውን አሰምተው ነበር፡፡

በ 2017/2018 የግብጽ ፕሪምየርሊግ ከወዲሁ ነጥቦችን መሰብሰብ ያልቻለው ዛማሌክ ከሜዳው ውጪ ተጉዞ ከታንታ ጋር 1-1 ተለያይቶ የተመለሰበት ጨዋታ ሌላው ውዝግብን የፈጠረ ሆኗል፡፡ባለሜዳዎቹ በመጀመሪያው ግማሽ የዛማሌኩ የመስመር ተከላካይ ሞአያድ አዛን በሰራው ጥፋት የፍጹም ቅጣት ምት ማግኘት ችለው ነበር፡፡ የዳኛው ውሳኔ በመልሶ እይታ እንደታየው ከሆነ ሶሪያዊው የዛማሌኩ የመስመር ተከላካይ ሞአያድ አዛን የታንታው ሞሀመድ ጋብር ጋር መጠነኛ ንክኪ እንደነበራቸው ተረጋግጧል፡፡

የዛማሌኩ ግብ ጠባቂ አህመድ ኤል ሺናዊ የፍጹም ቅጣት ምቱን ካዳነ በኋላ ዛማሌኮች ለጎል የቀረቡ አጋጣሚዎችን መጠቀም አልቻሉም፡፡ከብዙ ጥረት በኋላ በእለቱ የመጀመሪያ ጨዋውን ያደረገው ሳላህ አሾር ዛማሌኮችን ቀዳሚ አደረገ፡፡

ነገርግን ባለሜዳዎቹ በመጨረሻው ደቂቃ ላይ ያገኙት ሌላ የፍጹም ቅጣት ምት ጨዋታውን በአቻ ውጤት እንዲያጠናቅቁ ቢረዳቸውም ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ብስጭት ውስጥ የገቡት የዛማሌክ ተጫዋቾች ከዳኛው ጋር እሰጣገባ ውስጥ ገብተው ታይተዋል፡፡

ለመግለጫ ፈጣን የሆኑት ሞርታዳ ማንሱርም እንደተለመደው የእለቱ ዳኛን በቡድናቸው ላይ ሴራ ማሴሩን በመናገር ከአሁን በኋላ ቡድናቸው በውጭ ዳኞች እንዲመራ ጥሪ አቀረቡ፡፡በተጨማሪም የግብጽ እግርኳስ ፌዴሬሽን የቦርድ አባላት ከሀላፊነታቸው እስካልወረዱ ድረስ ዛማሌክን ከሊጉ ውድድር ተሳትፎ ውጪ እንደሚያደርጉት ተናገሩ፡፡

የቡድኑ ደካማ አጀማመር በዚህ ብቻም አላበቃም በሜዳቸው በሰሞሀ 3-0 ሲሸነፉ የተለመደው የሞርታዳ ማንሱር ምክንያት ምን ሊሆን እንደሚችል ብዙዎቹ ሲጠበቁት ነበር፡፡በጨዋታው 18 የጎል እድሎችን አግኝተው በተጫዋቾቻቸው ድክመት ጎል ማስቆጠር ያልቻሉት ዛማሌኮች ምክንያት አድርገው ያቀረቡት ነገር እጅግ አስገራሚ ነበር፡፡

ከጋዜጠኞች ፊት ሀሳባቸውን እንዲሰጡ የተጠየቁት ሞርታዳ ማንሱር በምላሻቸው “ዛሬ ሁሉም ተጨዋቾቻን እና አሰልጣኙ ጥሩ ነበሩ ነገርግን ከጎል ፊትለፊት ሆነህ 18 ጎል መሳት ጤናማነት ነው?ነገሮች በሚገባው መንገድ አልሄዱም፣ በጨዋታውን የተሸነፍነው በአስማት ነው፡፡” በማለት “አስማትን” ለሽንፈቱ ተጠያቂ አድርገዋል፡፡

አወዛጋቢው ሰው ባለፉት ሶስት አመታት ዛማሌክ ከግብጽ ፕሪምየርሊግ ውድድር ውጪ እንደሚሆን ዘጠኝ ጊዜ በመግለጫቸው አሳውቀዋል፡፡27 ጊዜ ደግሞ ዳኛን ወይንም እግርኳስ ፌዴሬሽኑን ምክንያት ሲያደርጉ አንድ ጊዜ ደግሞ ምክንያታቸው “አስማት” ሆኗል፡፡

ሞርታዳ ማንሱር ከዛማሌክ ጽንፈኛ ደጋፊዎች ጋር ያላቸው ግኑኝነት አሁንም ድረስ ጤናማ ባለመሆኑ ተቃውሞ በተለያ መንገድ ሲቀርብባቸው ይሰማል፡፡በተለይ በአንድ ወቅት “እነሱ ደጋፊዎች አይደሉም አሸባሪዎች ናቸው፡፡” ብለው ከተናገሩ በኋላ በተለያዩ ማህበራዊ ሚድያዎች ደጋፊዎች ከክለባቸው እንዲወጡላቸው ደጋግመው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ያ ካልሆነ ግን ሊገድሏቸው እንደሚችሉ ተዝቶባቸዋል፡፡

5
ጽንፈኞቹ የዛማሌክ ደጋፊዎች አሁንም ከሞርታዳ መንሱር ጋር እሳትና ጭድ ናቸው::

እነዚህ ጽንፈኛ ደጋፊዎች የክለቡ ዋና ጽህፈት ቤት ድረስ በማቅናትና ጥቃት በመፈጸም በፕሬዝዳንቱ ሞርታዳ ማንሱር ላይ የግድያ ሙከራ ለማድረግ የሞከሩ ሲሆን በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው በህግ ተፈርዶባው ለእስር የተዳረጉም ይገኛሉ፡፡

ትእግስት አልባው ሊቀመንበር ከአሰልጣኞች ጋርም ያለቻው ቅርበት እምብዛም ነው፡፡ውሳኔያቸው ፈጣን እና ይዞት የሚመጣው መዘዝን ያገናዘበ አይደለም፡፡2016 ላይ በአንድ አመት ውስጥ ከ አምስት አሰልጣኞች በላይ ቀያይረዋል፡፡ከነዚህ ውስጥ የቀድሞ ሬንጄርስ እና የስኮትላድ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበሩት አሌክስ ማክሊሽ በ65 ቀናት እንዲሁም አህመድ ሚዶን በ 37 ቀናት ውስጥ ከዛማሌክ አሰልጣኝነት ያሰናበቱበት ትእግስት አልባ ውሳኔያቸው ይጠቀሳል፡፡

ሞርታዳ ማንሱር ፖርቹጋላዊው ኢናቺዮን  ሲያሰናብቱ በመካከላቸው የተፈጠረው አለመግባባት ትልቅ ሚና ነበረው፡፡ቡድኑ በግብጽ ፕሪምየርሊግ ሶስተኛ ደረጃን በማጠናቀቁ በዚህ አመት ግብጽን ወክሎ በቻምፕየንስ ሊጉ ላይ መሳተፍ አይችልም፡፡

አሰልጣኙ ከክለቡ የለቀቁ እንደ ሙስጠፋ ፋቲ እና ስታንሌ ኦቻውቺ ቡድኑን እደጎዱት በምክኒያትነት ቢያቀርቡም ምላሹን የሰጡት የክለቡ ሊቀመንበር ተጫዋቾቹ ከክለቡ የለቀቁት በአሰልጣኑ ጥያቄ እንደሆነ አስምረው ተናግረዋል፡፡

ይህም አሰልጣኝ ኢናቺዮ ያበሳጨ አስተያየነት ስለነበረ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ “ሞርታዳ ማንሱር የተናገሩት ውሸት ነው” ብለው ከተናገሩ በኋላ የእርስ በርስ ግጭቱ ከሮ ከክለቡ ጋር ለመለያየት በቅተዋል፡፡

ሞንቲኔግሯዊው አሰልጣኝ ኒቦሳ ጆቮቪችን ባለፈው ነሀሴ ወር ላይ የቀጠረው ዛማሌክ እኚህን አሰልጣኝ ደግሞ ከስንት ቀን በኋላ ይባረሩ ይሆን?የሚለው ጥያቄ በአወራራጅ ተቋማት ጭምር ትኩረት የተሰጠው ሆኖ ቆይቷል፡፡ቆይታቸውም ግን እስከ በፈረንጆቹ አዲስ አመት መግቢያ ብቻ ነበር፡፡ቡድኑ በኤል ጋይሽ ከተሸነፈ በኋላ የስንብት ደብዳቤ ተሰጥቷቸዋል፡፡

9.jpg

ክለቡ ብዙ ሚሊየን ፓውንዶችን ለአዳዲስ ተጫዋቾች ያወጣ ቢሆንም ውጤት ጀርባዋን ሰጥታቸው አሁንም ከባላንጣቸው አል አህሊ በታች ተቀምጠዋል፡፡ትእግስት አልባው ሞርታዳ መንሱርም ከአወዛጋቢ ምክንያታቸው ጋር ከቡድኑ ጋር ጉዟቸውን ቀጥለዋል፡፡ባለፈው ህዳር ወርም በድጋሚም የዛማሌክ ፕሬዝዳንት ሆነው እስከ 2022 እንዲቀጥሉ ተመርጠዋል፡፡

 

 

 

 

Advertisements