አሌክሲስ ሳንቼዝ / የቺሊያዊ አጥቂ የዝውውር ሂደት እና የእንግሊዝ ጋዜጦች ዝውውሩን የተመለከተ ዘገባ ልዩ የዳሰሳ ጥንቅር

በ 2014 አርሰናልን በ 35 ሚሊዮን ፓውንድ የተቀላቀለው እና የኢምሬትስ ቆይታው በመጪው ክረምት የሚያበቃው ሳንቼዝ ካሳለፍነው ክረምት ጀምሮ ከአርሰናል እንደሚለቅ በትልቁ ሲነገር ቆይቷል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም በቀድሞ አሰልጣኙ ፔፕ ጋርዲዮላ ወደሚሰለጥነው ማንችስተር ሲቲ የማምራት ፍላጎት እንዳለውና የኢትሀዱ ክለብም ፈላጊው እንደሆነ ከታወቀ ዋል አደር ብሏል።

ነገርግን በትናንትናው ዕለት የጆሴ ሞውሪንሆው ማንችስተር ዩናይትድ የአጥቂ መስመሩን በቺሊያዊው ኮከብ ይበልጥ ለማጠናከር እና የፊት መስመር ተጫዋቾቹን ቁጥር ለመጨመር ማሰቡንና የሚያሳብቅ መረጃ ተሰምቷል።

በመረጃው መሰረትም ዩናይትድ ለሳንቼዝ 25 ሚሊዮን ፓውንድ ሂሳብና በኦልትራፎርድ የተገፋውን ጨዋታ አቀጣጣይ ሄነሪክ ማኪቴሪያን የውል ስምምነቱ አካል በማድረግ ለአርሰናል በመስጠት የ 29 አመቱን ተጫዋች በእጁ ለማስገባት እና ጎረቤቱን ለመቀናቀን ማሰቡ ታውቋል።

እነዚህ ሁሉ ነገሮች የተጨማመሩበትና ውክብክብ ያለው የሳንቼዝ መጨረሻም 19 ቀናት የቀሩት የዝውውር መስኮት በአንዱ ቀን ቁርጡ እንደሚታወቅ ይታመናል። እስከዛው ድረስ ግን ከክለቡ እንደማይለቅ በአርሰን ቬንገር እየተወራለት ያለውን ተጫዋች በተመለከተ የጋዜጦችንና የዜና ተቋማትን መረጃ በጥሞና መቃኘቱ መልካም ይመስላል። 

የኢትዮአዲሱ ሚኪያስ በቀለም የእንግሊዝ የህትመትና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚከተለው በወፍ በረር ያስቃኘናል። 


በቀዳሚነት የምንመለከተው ዴይሊ ስታር የተሰኘው ጋዜጣ በዛሬው ዕትሙ የቺሊያዊው አጥቂ የቡድን አጋሮች ወደማንችስተር ማምራቱ እንደማይቀር ላቀረቡለት ጥያቄ ሳንቼዝ “የትኛው ማንችስተር” ሲል ጥያቄያቸውን በጥያቄ መመለሱን እና አርሰናል በበኩሉ ዩናይትድ በዝውውር ድርድሩ ላይ አንቶኒ ማርሻልን ሊካተት ይችል እንደሆነ ጥያቄ ማቅረቡን አያይዞ ፅፏል። 

የእንግሊዙ የዜና ወኪል ቢቢሲ ደግሞ አርሰናል ለአጥቂው ተስማሚ የዝውውር ዋጋ ከቀረበለት እና ምትክ የሚሆነውን ተጫዋች እንደሚያገኝ ካረጋገጠ በዚህ በያዝነው ጥር ሳንቼዝን እንደሚሸጥ ገልጾ በምትክነትም የቦርዶክሱ ባለተሰጥኦ ታዳጊ ማልኮም ትልቅ ግምት እንዳገኘ አትቷል።

ሚረር በበኩሉ ሳንቼዝ በጠየቀው 400,000 ፓውንድ ሳምንታዊ ደሞዝ እና 15 ሚሊዮን ፓውንድ የፊርማ ክፍያ የተነሳ ሲቲ ዝውውሩን ለማድረግ ፍቃደኛ እንዳልሆነ ፅፏል። 

በሌላ በኩል ታማኙ የእንግሊዝ ጋዜጣ ዘቴሌግራፍ ሳንቼዝ በዚህ ጥር በዩናይትድ የቅድመ ዝውውር ጥናት የተደረገበት የመጀመሪያው አጥቂ እንዳልሆነና ጆሴ ሞውሪንሆ የቀድሞውን የኦልትራፎርድ ተወዳጁ ዣቪ ኸርናንዴዝ ከሌስተሩ ጂሚ ቫርዲ ጋር በዝውውር ኢላማ ስም ዝርዝራቸው ውስጥ እንዳካተቱ ያተተበትን ዘገባ ይዞ ወጥቷል።

ጋዜጣው በዘገባው ቫርዲ ዋጋው 35 ሚሊዮን ፓውንድ የሚደርስና ውድ በመሆኑ ኸርናንዴዝ ወደዩናይትድ ለመምጣት የቀረበ ተጫዋች መሆኑን ጨምሮ ፅፏል።

ዴይሊ ሜይል በበኩሉ ሞውሪንሆ ዝውውሩ እንዲሳካ ሄነሪክ ማኪቴሪያንን የድርድሩ አካል በማድረግ ለአርሰናል ለመስጠት አይናቸውን እንደማያሹ ያወሳበትንና በትናንትናው ዕለት ስካይ ስፖርትን የመሰሉ ታማኝ የዜና ምንጮች በትልቁ ሲያወሩት እና ሲገርቡት ያደሩትን ዘገባ በጠዋት ይዞ ብቅ ብሏል።

በዕለተ ጁማ ሳንቼዝን የዘገባው አንድ አካል አድርጎ የተከሰተው ሌላኛው የእንግሊዝ ጋዜጣ የቴሌግራፍ አምሳያውና በዘገባው እውነታነት እና ጥራት የማይታማው ምንም የሚጣል መረጃ የሌለው እንከነ ቢሱ ዘጋርዲያን ነው። 

ዘጋርዲያን በጀርባ ገፁ ባሰፈረው መረጃ ሳንቼዝ ከሲቲ ጋር በሳምንት 250,000 ፓውንድ የሚያስገኝለትን የግላዊ ስምምነት ማጠናቀቁን ነገርግን ጆሴ ሞውሪንሆ ፍልሚያውን በድል እንደሚያጠናቅቁ የራስ መተማመን መንፈስ ላይ እንደሆኑ አትቷል። 

በመጨረሻም የተጎዳን ሞተ ማለት የሚቀናው የፓፓራዚዎች ስብስቡ ዘሰን ቺሊያዊው ኮከብ ልቡ በባርሴሎና ያሰለጠኑትን ፔፕ ጋርዲዮላ ለመቀላቀል እየዋለለ መሆኑን ነገርግን ሲቲ ዝውውሩን ማጠናቀቅና ሳንቼዝን በእጁ ማስገባት ከፈለገ የዝውውር ሂሳቡን ወደ 35 ሚሊዮን ፓውንድ ማናር እንዳለበት ፅፏል።

እናም ውድ የኢትዮአዲስ አንባቢያን ከአሌክሲስ ሳንቼዝ ችኮ የዝውውር ሂደት ጋር በተያያዘ የዕለቱን የጋዜጦች ዘገባ ከቀደምት ባህሪያቸውና የታማኝነት ደረጃቸው አንፃር በዝርዝር ነግረናችኋል። የተመቻችሁን ዘገባ እያነሳችሁ ያልተመቻችሁን እየጣላችሁ ከራሳችሁ ጋር ተወያዩበት። 

Advertisements