ሽንፈት / ማንችስተር ሲቲ በአሌክሲስ ሳንቼዝ ዝውውር ዙሪያ እጅ ለመስጠት መቃረቡ ተገለፀ

  

ማንችስተር ሲቲ በአርሰናል እና በአሌክሲስ ሳንቼዝ የተጠየቀው ዋጋ እጅግ የተጋነነ እንደሆነ በማሰቡ ቺሊያዊውን አጥቂ የማስፈረሙ ነገር የሞተ እንደሆነ ለመቀበል ትንሽ እንደቀረው ተገለፀ።  

ሲቲ ለዝውውሩ ያዘጋጀውን 20 ሚሊዮን ፓውንድ ለመጨመር እንዳሰበ ቢታሰብም በቀጣይ ክረምት የውል ስምምነቱ ከሚጠናቀቀው ተጫዋች እና ወኪሉ ፍሊሴቪች የተጠየቀው ገንዘብ ወደኋላ እያሸሸው እንደሆነ ታውቋል። 

በዛሬው ዕለትም ፔፕ ጋርዲዮላ፣ የክለቡ ስፖርት ሀላፊ ቲኪ ቤግሪስታይን፣ ዋና ስራ አስፈፃሚው ፌራን ሶሪያኖ እና ሊቀመንበሩ ካልዱን አልሙባረክ በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት እንደሚያደርጉ የተገለፀ ሲሆን የኢትሀዱ ክለብ አቋም የመቀየሩ ነገር ግን የማይሆን እንደሆነ ተሰምቷል። 

ይህ ሁኔታም ማንችስተር ዩናይትድ ለተጫዋቹ የተጠየቀውን የዝውውር ሂሳብ የሚያቀርብ ከሆነ የ 29 አመቱን ተጫዋች እንዲገዛ መንገዱን እንደሚያመቻችለት እና የክለቡ ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢውድ ውድዋርድ እስከ 35 ሚሊዮን ፓውንድ ሊያቀርቡ እንደሚችሉ ተነግሯል።

ሲቲ ከሳንቼዝ እና ከወኪሉ ጋር ካሳለፍነው ክረምት በፊት ጀምሮ ድርድር ሲያደርግ ቢቆይም ባሳለፍነው ሳምንት ሁለቱም ከዝውውሩ የሚፈልጉትን ሂሳብ መጨመራቸውን ለኢትሀዱ ክለብ አሳውቀዋል። 

ከዚህ ጋር በተያያዘም የፕሪምየር ሊጉ መሪዎች ተጫዋቹን የማግኘታቸው ነገር የተበበ እንደሆነ እንዲያስቡ እንዳደረጋቸው ተያይዞ ተወስቷል። 

Advertisements