“ከጆርጂዮ ቺሊኒ ክስተት በኋላ ባርሴሎና ሲፈልገኝ አልቅሻለሁ” – ሊውስ ሱዋሬዝ 

ሊውስ ሱዋሬዝ በ 2014 አለም ዋንጫ ጆርጂዮ ቺሊኒን ከነከሰ በኋላ የባርሴሎና ዝውውሩ እንደማይሳካ በማሰብ ጭንቀት ውስጥ ገብቶ እንደነበር እና የካታላኑ ክለብ ፍላጎቱን ባለማንሳቱም በወቅቱ በደስታ ማንባቱን ገልጿል። 

በወቅቱ ኡራጋዊው ተጫዋች ለአራት ወራት ከማንኛውም የእግር ኳስ እንቅስቃሴ ሲታገድ በአለም አቀፍ ጨዋታዎች ላይ የዘጠኝ ጨዋታዎች ቅጣት ተላልፎበት እንደነበር አይረሳም። 

በ 2010 አለም ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ ከጋና ጋር በነበረው ጨዋታ ከጎል ሳጥን ውስጥ ኳስን በእጁ አውጥቶ ሀገሩ ወደግማሽ ፍፃሜ እንድታልፍ ያደረገው አወዛጋቢው አጥቂ በብራዚሉ አለም ዋንጫ ሀገሩ ኡራጋይ ጣሊያንን 1-0 በረታችበት የምድቡ የመጨረሻ የአዙሪዎቹን ተከላካይ በመንከስ ከስፖርታዊ ያፈነገጠ ስራን ሰርቷል። 

ከዛ ቀደም ሱዋሬዝ በአያክስ እና በሊቨርፑል ተጫዋችነቱ የተቃራኒ ተጫዋቾች ላይ ንክሻን ፈፅሞ የነበረ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ለሶስተኛ ተመሳሳይ ጊዜ ድርጊቱን መፈፀሙ ተጫዋቹ በትልቁ እንዲብጠለጠል ምክንያት ሆኖ አልፏል።

በወቅቱ የተፈጠረው ሁኔታ ግን ባርሴሎና 75 ሚሊዮን ፓውንድ ለሊቨርፑል ከፍሎ ሱዋሬዝን ከማምጣት ያላገደው ሲሆን ኡራጋዊው ኮከብም በኒውካምፕ ቆይታው ሁለት የላሊጋ፣ ሶስት የኮፓ ዴላሬይ፣ አንድ የቻምፒዮንስ ሊግ እና አንድ የአለም ክለቦች ዋንጫን ማግኘት ችሏል።

ሱዋሬዝ ከአራት አመታት በፊት የነበረውን ሁኔታ በተመለከተ ተጠይቆም “ድርጊቱን ከፈፀምኩ በኋላ ወዲያው ያደረኩትን ነገር አሰብኩኝ። ከትንሽ ቆይታ ማለትም ከአስር ደቂቃ በኋላ መሰለኝ ዲያጎ ጎዲን ግብ አስቆጠረ። 

“እያንዳንዱ ሰው ሲደሰት እኔ በተለመደው መልኩ ደስታዬን መግለፅ አልቻልኩም። ምክንያቱም እኔ እያሰብኩ የነበረው በቀጣይ ሊፈጠር የሚችለውን ነገር ነበር። ከዛም ወደመልበሻ ክፍል ገባሁና መጀመሪያ ያደረኩት ነገር ልጆቻችን ይዛ በእዛ የነበረችውን ባለቤቴን ማናገር ነው።

“እሷም ምን እንደፈፀምኩ ጠየቀችኝ። በእርግጥ ሁሌም በመጀመሪያ ነገሮችን ለመቀበል አልፈልግም። ቀድሞኝ በውስጤ የሚመጣው አሉታዊ ነገር፣ ለቅሶ እና መሰል ነገር ነው። ከዛ ግን በመልበሻ ቤት ውስጥ የደስታ ስሜት ተፈጠረ። ሁሉም ግን ባደረኩት ነገር ምን ይፈጠር ይሆን በሚል ስልካቸውን እየጎረጎሩ ነበር።” ሲል ሁኔታውን አስታውሷል።

በመቀጠልም ወደባርሴሎና ያደረገው ዝውውር ላይሳካ ይችል እንደሆነ በማሰብ ተጨንቆ እንደሆን ሲጠየቅ “አዎ! አዎ!” ሲል መለሰ። 

ሱዋሬዝ ንግግሩን በመቀጠልም “ምክንያቱም ስለአለም ዋንጫው ቆይታዬ ከማሰብ በተጨማሪ ወደባርሴሎና የመሄድ ህልሜ እና ሁሉም ነገር እንዳበቃ ነው ያሰብኩት። 

“ድርጊቱን ከፈፀምኩ ጥቂት ቀናት በኋላ እና ከአለም ዋንጫው ከመባረሬ በፌት ከአዶኒ ዙቢዛሬታ እና ከክለቡ (ባርሴሎና) ፕሬዝዳንት ጋር አውርቼም እንድረጋጋና ባርሴሎና አሁንም (ከንክሻው በኋላም) እንደሚፈልገኝ ነገሩኝ። ከዛም አለቀስኩ።

“ምክንያቱም በወቅቱ ከፈፀምኩት አስቀያሚ ነገር አንፃር በእኔ ላይ እምነት ማሳደር የማይቻል ነበር። እውነታው ባርሳ ለእኔ በጣም ጥሩ ነበር። ሁልጊዜም ለእዛ ሁኔታ ምስጋና አለኝ።” በማለት በድንገት የፈፀመው ያልተገባ ተግባር ያስከፈለውን መስዋትነት በዝርዝር አስረድቷል። 

ሱዋሬዝ በትናንትናው ዕለት ባርሴሎና ለሰባት ተከታታይ ጨዋታ ማሸነፍ ወዳልቻለበት የሪያል ሶሲዳድ ሜዳ አምርቶ የኤርነስቶ ቫልቬርዴን ልጆች 4-2 ሲረታ ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።

Advertisements