“ሪያል ማድሪድ ሮናልዶን መሸጥ ቢፈልግም የማንችስተር ዩናይትድ ፍላጎት የተወሳሰበ ነው” – ሂሌም ባላጉ


ሪያል ማድሪድ ክርስቲያኖ ሮናልዶን ለመሸጥ ዝግጁ ቢሆንም በፖርቹጋላዊው ኮከብ ዝውውር ዙሪያ የማንችስተር ዩናይትድ ፍላጎት የተወሳሰበ እንደሆነ ሂሌም ባላጉ ገለፀ፡፡ 

የስፔኑን ተአማኒ የስፖርት ተንታኝ የሆነው ባላጉ በእንግሊዙ የዜና ወኪል ስካይ ስፖርት ባሰፈረው ፅሁፍ ፖርቹጋላዊው የአምስት ጊዜያት የባለንዶር አሸናፊ በአዲስ የውል ስምምነት ዙሪያ የተገባለት ቃልኪዳን ባለመጠበቁ ደስተኛ እንዳልሆነና የዘጠኝ አመት የበርናባው ቆይታው ሊያበቃ መቃረቡን አትቷል፡፡

ሮናልዶ በተደጋጋሚ ጊዜ ወደዩናይትድ እንደሚያመራ ሲነገር የቆየ ቢሆንም የኦልትራፎርዱ ክለብ ከተጫዋቹ ከፍተኛ የዝውውር ሂሳብ አንፃር ጥንቃቄ መውሰድ መምረጡን በዘገባው ተያይዞ ተገልጿል፡፡ 

ባላጉ ጉዳዩን ሲያስረዳም “የሮናልዶ መልዕክት መልቀቅ መፈለጉ ሲሆን ሪያል ማድሪድም ሊሸጠው ይፈልጋል፡፡ ነገርግን ማድሪድ ተጫዋቹን ለማዘዋወር ፒኤስጂና ማንችስተር ዩናይትድ እንዲፋለሙ ይሻል፡፡ ነገርግን ጉዳዩ ተጫዋቹን ከመፈለግ በዘለለ ውስብስብ ነው፡፡ 

“ዝውውሩን ለማድረግ ለሮናልዶ አመታዊ የ 44 ሚሊዮን ፓውንድ ደሞዝ ያስፈልጋል፡፡ ማድሪድ በበኩሉ 33 አመት ሊሆነው ለተቃረበ ተጫዋች ውድ የሆነ 89 ሚሊዮን ፓውንድ የሚጠጋ የዝውውር ሂሳብ ይፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል እዚህ ላይ የዩናይትድ ሁለት ተቃራኒ እይታ አለ፡፡ 

“የኦልትራፎርዱ ክለብ ሮናልዶ እንደሚሸጥ ካረጋገጠ በተጫዋቹ ላይ ፍላጎት አለማሳየት አይችልም፡፡ ነገርግን ለተጫዋቹ ዝውውር የሚጠየቀው ከፍተኛ ገንዘብ አሳማኝ አይደለም፡፡ 

ሮናልዶ በዘንድሮው የውድድር ዘመን በላሊጋው ለክለቡ ሪያል ማድሪድ ማስቆጠር የቻለው አራት ግቦችን ብቻ ሲሆን ቡድኑም ከሊጉ መሪው ባርሴሎና በትልቅ የነጥብ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ 

ከዚህ ጋር በተያያዘም የስፔኑ ክለብ ራሱን ለማደስ ሲል ሮናልዶን ሊሰዋ እንደሚችል ባላጉ አስረድቷል፡፡ “ከዚህ ቀደም እንደተናገርኩት ችግሩ (የሮናልዶ) ጎል አለማስቆጠሩ ብቻ አይደለም፡፡ 

“ባለፉት አመታት እንደተናገርኩት በአካል ብቃት ደረጃ ጥግ ላይ ደርሷል፡፡ ይህን ማለቴም የጎል ማግባት ሂደቱ ዳግም ሲመጣ ግብ ማስቆጠሩን ይቀጥላል፡፡ ነገርግን በጨዋታዎች ላይ ያለው ጫና ቀንሷል፡፡ 

“ምንም እንኳን ከቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ በኋላ አዲስ የውል ስምምነት እንደሚቀርብለት ቃል የተገባለት ቢሆንም ያንን ማግኘት አልቻልም፡፡ የመጨረሻ የማድሪድ ቤት የውል ስምምነቱን ሕዳር 2016 ከመፈራረሙ ጋር በተያያዘም ማድሪድ የተጫዋቹን ሰምምነት የማራዘም ፍላጎት ያለው አይመስልም፡፡” ሲል ሀሳቡን ቋጭቷል፡፡ 

ፖርቹጋላዊው ኮከብ በ 2009 ዩናይትድን ለቆ ወደስፔን ካመራ ወዲህ በበርናባው ቆይታው በ 418 ጨዋታዎች ላይ 422 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፡፡ 

Advertisements