ሽኝት / ቲዮ ዋልኮት የኤቨርተን ዝውውሩን ለማጠናቀቅ ለህክምና ምርመራ ወደመርሲሳይድ አመራ

ቲዮ ዋልኮት ክለቡ አርሰናልን ለቆ ወደ ኤቨርተን የሚያደርገውን ዝውውር ለማጠናቀቅ ለህክምና ምርመራ ወደመርሲሳይድ አምርቷል። 

የእንግሊዝ ታማኝ የዜና ተቋም የሆነው ስካይ ስፖርት እንደፃፈው ከሆነ ዋልኮት የጉዲሰን ፓርክ ዝውውሩን ለመፈፀም ሲል የህክምና ምርመራውን ለማድረግ ከትንሽ ደቂቃዎች በፊት የኤቨርተን የልምምድ ማዕከል ፊንች ፋርም መገኘቱም ተረጋግጧል። 

የእንግሊዛዊው የክንፍ ተጫዋች የዝውውር ሂሳብ 20 ሚሊዮን ፓውንድ እንደሚገመት የተነገረ ቢሆንም ገና ድርድሮች እንዳልተቋጩና ቁርጥ የዝውውር ሂሳቡ እንዳልታወቀ ተገልጿል። 

ባሳለፍነው ሳምንት የኤቨርተኑ አለቃ ሳም አላርዳይስ ቶፊዎቹ በ 2006 ሳውዝአምፕተንን ለቆ ወደኢምሬትስ በመጣው ዋልኮት ሽያጭ ዙሪያ ድርድር መጀመራቸውን ገልፀው እንደነበር አይዘነጋም። 

የዋልኮት የቀድሞ ክለብ የሆነው ሳውዝአምፕተን እንግሊዛዊውን ተጫዋች የማስፈረም ፍላጎት የነበረው ቢሆንም ኤቨርተን የ 28 አመቱን ተጫዋች የማስፈረም ፍልሚያ በድል መወጣቱ እርግጥ መስሏል።

የመርሲሳይዱ ክለብ የገንዘብ አቅም እና ዋልኮት ከአላርዳይስ ጋር መስራት መፈለጉ ወደሰሜን ምዕራብ እንግሊዙ ክለብ እንዲያመራ ሊያደርገው ከጫፍ መድረሱ ተያይዞ ተገልጿል።

ኤቨርተን በዚህ በያዝነው የዝውውር መስኮት ቱርካዊውን ሴንክ ቶሱን ከቱርኩ ቤሽኪሽታሽ በ 27 ሚሊዮን ፓውንድ ሂሳብ ማስፈረም የቻለ ሲሆን የዋልኮት መምጣትም ለክለቡ ስብስብ ትልቅ ጭማሪ እንደሆነ አላርዳይስ ተስፋ አድርገዋል።

Advertisements