“የሳንቼዝ ዝውውር የሚወሰነው በሚኪታሪያን ዝውውር ነው” – ሚኖ ራዮላ

በፖል ፖግባ ፣ ዝላታን ኢብራሒሞቪች ፣ ሄነሪክ ሚኪታሪያንና ሮሜሉ ሉካኩ የዩናይትድ ዝውውር ላይ የአንበሳውን ድርሻ የተወጣው ዝነኛው ወኪል ሚኖ ራዮላ እንደተናገረው ማንችስተር ዩናይትድ አሌክሲስ ሳንቼዝን የግሉ ለማድረግ ወሳኝ የሆነው የአርሜንያዊው ዝውውር ሆኗል፡፡

እንደወኪሉ ገለፃ ይህንን የዝውውር ውጥን ከወጠነ ስድስት ሳምንታትን ያስቆጠረ ሲሆን ዕቅዱም ያለምንም ተጨማሪ ገንዘብ በሁለቱ ተጫዋቾች መካከል የሚደረግ ቀጥተኛ ልውውጥ ነው፡፡

ለረጅም ጊዜ ከቺሊያዊው ጋር ስሙ ሲያያዝ የቆየው ማንችስተር ሲቲ ከተጫዋቹ ድርድር እጁን ማውጣቱን ተከትሎ ቀያዮቹ ሰይጣኖች በዝውውሩ ጉዳይ ላይ መሪ ተዋናይ ሆነው ቢቀርቡም ይህ ግን እውን ሊሆን የሚችለው በአንድና አንድ ቅድመ ሁኔታ መሆኑን የገለፀው ራዮላ ይህ ቅድመ ጉዳይም የሚኪታሪያን የሰሜን ለንደን ጉዞ ነው፡፡

ራዮላ ሲናገር “የሚኪ የማንችስተር ዩናይትድ ቆይታ ችግር የጨዋታ ጊዜ የማግኘት ችግር ብቻ ነው ፤ ከአሰልጣኙ ጋር ሌላ የተለየ ፀብ የለውም፡፡ ይህ ለአርሰናል ትልቅ ዕድል ነው፡፡ በወጣት ኮከብ ተጫዋች ቡድኑን ማደስ ይችላል፡፡ ስለሆነም የሳንቼዝ ዝውውር ሊሳካ የሚችለው የሚኪ ወደለንደን መሄድ እውን ሲሆን ብቻ ነው” ብሏል፡፡

ከማንችስተር ዩናይትድ በተጨማሪ በቼልሲና በሊቨርፑል ተፈላጊ እንደሆነ የተነገረለት ሳንቼዝ ከአርሰናል ጋር ያለው እህል ውሃ ወደፍቺ የተቃረበ ሲሆን ከማንችስተር ዩናይትድ ጋር የሚካሄደው ድርድር ከተሳካ ያለምንም ተጨማሪ ገንዘብ በተጫዋች ልውውጥ ብቻ እንደሚከወን ተሰምቷል፡፡

Advertisements