ሮናልዲንሆ እግርኳስ መጫወት ማቆሙን ወኪሉ ገለፀ

የቀድሞው ባርሴሎናና የኢንተርሚላን ተጫዋቹ ብራዚላዊው ሮናልዲንሆ ጎቾ እግርኳስ መጫወት ማቆሙን ወኪሉ በይፋ ገልፅዋል።

በእግርኳስ ተጫዋችነት ዘመኑ ስኬታማ ጊዜያትን ያሳለፈው ሮናልዲንሆ ጫማውን ለመስቀል ውሳኔ ላይ የደረሰው በ37 ዓመቱ ነው።

በ2015 የብራዚሉን ክለብ ፍሉሚኔንዜን ከለቀቀ በኋላ ከኮንትራት ነፃ ሆኖ የነበረው ሮናልዲንሆ እግርኳስ መጫወት የሚችልበት ሌላ ክለብ ማግኘት ሳይችል ቀርቷል።

እናም የሮናልዲንሆ ወኪል እና ወንድም የሆነው ሮቤርቶ አሲስ ተጫዋቹ ጨዋታ የማቆሙን ዜና ይፋ አድርጓል።

አሲስ ብራዚላዊውን ታሪካዊ ተጫዋች ከእግርኳስ ጨዋታ የሚያደረገውን የክብር ስንብት ከሩሲያው የዓለም ዋንጫ መጠናቀቅ በኋላ በልዩ ሁኔታ ለማሰናዳት ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም ገልፅዋል።

“እግርኳስ አቁሟል። አብቅቷል።” ሲል አሲስ ለብራዚሉ ኦ ግሎቦ ጋዜጣ ተናግሯል።

“[ለስንብቱም] ከሩሲያው የዓለም ዋንጫ በኋላ ምን አልባትም በነሃሴ ወር የሆነ ነገር እና የሚገባውን ትልቅ ነገር የምናዘጋጅለት ይሆናል።

“በብራዚል፣ በአውሮፓና በእሲያ አንዳንድ ዝግጅቶችን የምናከናውንም ይሆናል።

“በእርግጥ ከብራዚል ብሄራዊ ቡድን ጋርም የሆነ ነገር ለማዘጋጀት አቅደናል።” በማለት አክሎ ተናግሯል።

ሮናልዲንሆ ከባርሴሎና ጋር እ.ኤ.አ. በ2006 ካነሳው የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ በተጨማሪ የላ ሊጋውን ዋንጫ ሁለት ጊዜ በማንሳት ወርቃማን የተጫዋችነት ዘመን ማሳለፍ ችሏል።

ተጫዋቹ ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር እ.ኤ.አ. በ2002 የዓለም ዋንጫን እንዲሁም የኮፓ አሜሪካን እና የኮንፌዴሬሽን ዋንጫዎችንም መሳም ችሏል።

Advertisements