ቆይታ / ጆሴ ሞውሪንሆ ለተጨማሪ አመታት በማንችስተር ዩናይትድ የሚያቆያቸውን የውል ማራዘሚያ ስምምነት መፈራረማቸው ተገለፀ 

ጆሴ ሞውሪንሆ በኦልትራፎርድ አሁን ካላቸው የሶስት አመት የውል ስምምነት በላይ በማንችስተር ዩናይትድ የሚያቆያቸውን አዲስ የውል ስምምነት ማራዘሚያ መፈራረማቸው ተገለፀ። 

የ 54 አመቱ የቀድሞ የቼልሲና የሪያል ማድሪድ አለቃ በውድድር ዘመኑ መክፈቻ ላይ በድንገት ስማቸው ከፈረንሳዩ ፒኤስጂ ጋር ተያይዞ የነበረ ሲሆን ወደፓሪሱ ክለብ እንደሚያመሩም መነገሩ ይታወሳል።

ነገርግን የቀያይ ሴጣኖቹ አለቃ ለክለባቸው ያላቸውን ታማኝነት ባሳበቀ መልኩ አዲስ የውል ስምምነት ማራዘሚያ እንደተፈራረሙና በቀጣዮቹ ጊዜያት የስምምነቱ ዝርዝር መረጃ ይፋ እንደሚደረግ ሜትሮ የተሰኘው የእንግሊዝ ጋዜጣ ዘናሽናልን ጠቅሶ ፅፏል።  

በዘገባው መሰረት ዩናይትድ በ 2019 ውላቸው ከሚያበቃው ፖርቹጋላዊው የክለቡ አለቃ ጋር በውል ማራዘሚያ ዙሪያ ያደረገውን ድርድር በስኬት ማጠናቀቁ ተያይዞ ተገልጿል።  

በሌላ በኩል ግን ከሚተገብሩት በመከላከል ላይ ያመዘነ አጨዋወት እና ዩናይትድን ወደቀደመ ስኬቱ ለመመለስ ብዙ የሚቀራቸው ከመሆኑ አንፃር ፖርቹጋላዊው አለቃ በብዙ የክለቡ ደጋፊዎች ተቃውሞ የሚቀርብባቸው ሲሆን አንዳንድ ደጋፊዎች ደግሞ ስንብታቸውን ለመስማት እንደሚፈልጉ በተደጋጋሚ ይጠቀሳል። 

ሞውሪንሆ በዩናይትድ በነበራቸው የመጀመሪያ የውድድር ዘመን የካራቦአ እና የኢሮፓ ሊግ ዋንጫን ለክለባቸው ማምጣት እንደቻሉ ግን አይዘነጋም። 

Advertisements