የዩናይትዱ ጄሲ ሊንጋርድ የሳንቼዝ ዝውውር ሊጠናቀቅ መቃረቡን የሚያመለክት ፍንጭ ሰጠ

የማንችስተር ዩናይትዱ የመስመር እና የአጥቂ አማካይ የሆነው ጄሲ ሊንጋርድ የአርሰናሉ አሌክሲስ ሳንቼዝ ወደ ዩናይትድ የሚያደርገው ዝውውር ሊጠናቀቅ መቃረቡን የሚያመለክት ፍንጭ ሰጥቷል።

አሌክሲስ ሳንቼዝ ከአርሰናል ጋር ያለውን ኮንትራት ሊጠናቀቅ ስድስት ወራት ብቻ መቅረቱን ተከትሎ ክለቡ በነፃ ተጫዋቹን እንዳያጣ በተከፈተው የዝውውር መስኮት መሸጥን ምርጫው አድርጓል።

ማን ሲቲ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ተጫዋቹን በ 60 ሚሊየን ፓውንድ ለማስፈረም እስከመጨረሻው ቢታገልም ተተኪ ተጫዋች ያላገኙት መድፈኞቹ ዝውውሩ እንዳይፈፀም አድርገውታል።

ሲቲዎች በተከፈተው የዝውውር መስኮት ተመልሰው ተጫዋቹን እንደሚያዘዋውሩት ቢጠበቅም ጎረቤታቸው ዩናይትዶች ሳይጠበቅ ፍላጎት በማሳየታቸው ዝውውሩ የተወሳሳበ አድርገውታል።

ጫን ያለ የዝውውር ሂሳብ ይዘው የመጡት ዩናይትዶች ሲቲዎችን ከፉክክሩ በማስወጣት ብቻቸውን በዝውውሩ ላይ ተደራድረው መቋጫውን ለማብሰር ተዘጋጅተዋል።

ቼልሲዎች ቢሆኑ የተጫዋቹ ፈላጊ እንደሆኑ ቢነገርም ጫን ብለው ፍላጎታቸውን ባለማሳየታቸው ለማን ዩናይትዶች መልካም አጋጣሚ ሆኖላቸዋል።

ጆሴ ሞሪንሆ ዝውውሩን ለማሳካት ሄነሪክ ሚኪቴሪያን ለአርሰናል ለመስጠት ጭምር ያቀረቡ ሲሆን ይህም ጥሩ ምላሽ እንዳገኘላቸው ታውቋል።

በዚህም መሰረት ሳንቼዝ ወደ ኦልድትራፎርዱ ክለብ ለማቅናት የመጨረሻው ምእራፍ ላይ እንደሚገኝ የታወቀ ሲሆን በቀጣዮቹ ሰአታትም ዝውውሩ ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል።

የክለቡ አማካይ ጄሲ ሊንጋርድ ደግሞ ዝውውሩ ሊጠናቀቅ የሚያመለክት ፍንጭ ዛሬ ጠዋት በኢንስታግራም አካውንቱ ገልፇል።

“ሄሎ፣እንኳን ደህና መጣችሁ፣ደህና ናችሁ?ጊዜያችሁን እዚህ እየተዝናናችሁ እንደሆነ አስባለው።በህክምና ምርመራውም ተዝናኑ!”

በማለት አሌክሲስ ሳንቼዝ የህክምና ምርመራ እያደረገ መሆኑን የሚያመለክት መልእክት ተናግሯል።

በምስሉ ላይ እንደሚታየው አዲዳስ 7 ቁጥር ማሊያን ማተም ጀምሯል

ሳንቼዝ በዩናይትድ ታሪካዊውን 7 ቁጥር ማሊያ እንደሚያደርግ የሚጠበቅ ሲሆን የክለቡም ከፍተኛ ተከፋይ እንደሚሆን ይጠበቃል።

Advertisements