“ማንችስተር ዩናይትድንና አሌክሲስ ሳንቼዝን እንኳን ደስ አላችሁ ልላቸው እወዳለሁ “- ፔፕ ጓርዲዮላ

ለረጅም ጊዜ ወደክለባቸው ማንችስተር ሲቲ ሊያመጡት ፈልገው ያልተሳካላቸውና በመጨረሻም ሳንቼዝ ወደከተማ ተቀናቃኛቸው ማንችስተር ዩናይትድ ሊዘዋወር መቃረቡን የተረዱት አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ በዝውውሩ እንዳልተከፉ እና ሁለቱንም አካላት እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡

ቺሊያዊው የፊት መስመር ተጫዋች አሌክሲስ ሳንቼዝ ካለፈው ክረምት የዝውውር መስኮት ጀምሮ ወደማንችስተር ሲቲ እንደሚያቀና ሲዘገብ የቆየ ቢሆንም በቅርቡ ዩናይትዶች ጣልቃ በመግባት የተጫዋቹን ዝውውር ለማጠናቀቅ እጅጉን መቃረባቸው እየተዘገበ ይገኛል፡፡
ማንችስተር ሲቲ ለሳንቼዝ የተጠየቀው የዝውውር ሂሳብ የተጋነነ መሆኑን በመግለፅ ከዝውውሩ ራሳቸውን ማግለላቸው የተዘገበ ሲሆን ፔፕ ስለጉዳዩ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ “የቁጥርና ሂሳብ ነክ ጉዳዮች ላይ ጎበዝ አይደለሁም ፤ እስካሁን እንደማውቀው ሳንቼዝ አሁንም የአርሰናል ተጫዋች ነው:: ወደዩናይትድ ለመሄድ የተቃረበ ይመስለኛል፡፡ ለዚህም ሁለቱንም አካላት እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ” ብለዋል፡፡

የሲቲው አለቃ አክለውም”ተጫዋቾች ሁሌም መጫወት የሚፈልጉበትን ቦታ የመምረጥ መብት አላቸው፡፡ ከሳንቼዝ ጋር በባርሴሎና ጥሩ ቆይታ ነበረን፡፡ መልካሙ ሁሉ ይግጠመው” ሲል ማጠቃለያ ሰጥተዋል፡፡

አርሰናልና ማንችስተር ዩናይትድ በሳንቼዝና በሄነሪክ ሚኪታሪያን መካከል ቀጥተኛ የተጫዋች ቅይይር ለማድረግ መቃረባቸው እየተዘገበ ይገኛል፡፡

Advertisements