ሮበን ቫንፐርሲ ወደልጅነት ክለቡ ተመለሰ

በ2004 አገሩን ለቆ ወደእንግሊዝ ከተጓዘ በኋላ በአርሰናልና በማንችስተር ዩናይትድ ድንቅ አመታትን ያሳለፈው ሆላንዳዊው የፊት አጥቂ ሮበን ቫንፐርሲ ወደልጅነት ክለቡ ፌይኖርድ ሮተርዳም ተመልሷል፡፡

በአሰልጣኝ ሉዊ ቫንሃል ተገፍቶ የኦልድትራፎርዱን ክለብ ከለቀቀ በኋላ በቱርኩ ፊነርባቼ ሲጫወት የቆየው ቫንፐርሲ በፊነርባቼ ኃላፊዎች የውል ስምምነቱን አቋርጦ ወደፈለገበት ክለብ እንዲሄድ ፈቃድ ማግኘቱን ተከትሎ የልጅነት ክለቡን መምረጡን ፌይኖርድ ሮተርዳም በይፋዊ ድረ ገፁ አሳውቋል፡፡

የ34 አመቱ ጨራሽ አጥቂ በእንግሊዝ ቆይታው ሁለት ጊዜ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ የጨረሰ ሲሆን በማንችስተር ዩናይትድም በአሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን እየተመራ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ መሳም ችሏል፡፡

ለሆላንድ ብሔራዊ ቡድን 102 ጊዜ መጫወት የቻለው ቫንፐርሲ ወደፌይኖርድ መመለሱን አስመልክቶ ክለቡ በድረ ገፁ “ቫንፐርሲን ወደቀድሞ ክለቡ ለመመለስ የከለከለው አንዳች ነገር የለም ፤ በግል ጉዳዮች ላይ ከስምምነት የተደረሰ ሲሆን የፊታችን ሰኞም በይፋ ፊርማውን የሚያኖር ይሆናል” ሲል አስፍሯል፡፡

Advertisements