አስደንጋጭ / ፔሌ በድንገተኛ የጤና እክል ምክንያት ሆስፒታል ገባ

የ 77 አመቱ የእግር ኳሱ አለም ምልክት ፔሌ በትንፋሽ ማጠር ምክንያት ራሱን በመሳቱ ሆስፒታል ገብቷል። 

የእንግሊዝ የእግር ኳስ ጋዜጠኞች ማህበር በዛሬው ዕለት እንዳስታወቀው ብራዚላዊው የእግር ኳስ ምጡቅ በደረሰበት ድንገተኛ የጤና መታወክ ትናንት ለሊት ላይ ወደሆስፒታል መግባቱ ታውቋል።

በመጪው እሁድ ለንደን ላይ ፔሌን ለእራት ግብዣ ጠርቶት የነበረው ማህበሩ ሁኔታው በከፍተኛ ድካም ምክንያት የተከሰተ መሆኑን ገልፆ ለቀድሞው የእግር ኳስ ኮከብ የፈጠነ መዳንን ተመኝቷል።

ፔሌ በአለም ዋንጫ ታሪክ (1958፣ 1962 እና 1970) ሶስት ዋንጫዎችን በማንሳት ቀዳሚ ሲሆን ከቅርብ አመታት ወደዚህ የጤናው ሁኔታ እያሽቆለቆለ የመሄድ ነገር አሳሳቢ ሆኖ ቆይቷል። 

በሙሉ ስሙ ኤዲሰን አራንተስ ዶናሲሜንቶ ተብሎ የሚጠራው ፔሌ ከህመሙ ጋር በተያያዘም ሀገሩ ባስተናገደችው የ 2016 የሪዮ ኦሎምፒክ ላይ የውድድሩን ችቦ እንኳን መለኮስ ሳይችል ቀርቷል። 

ፔሌ በከፍተኛ ደረጃ የሽንጥ ህመም የሚያስቸግረው የነበረ ሲሆን በ 2018 አለም ዋንጫ የእጣ ማውጣት ስነስርዓት ላይም በተሽከርካሪ ወንበር ላይ ሆኖ ከነቭላድሚር ፑቲን እና ዲያጎ ማራዶና ጋር የስነስርዓቱ ድምቀት ነበር። 

ብራዚላዊው የሜዳ ላይ ንጉስ በ 2014 በገጠመው የሽንት ቧንቧ መቁሰል (infection) ምክንያት ትንፋሹ ቀጥ በማለቱ የልዩ ህክምና ክትትል ክፍል እንዲገባ ተደርጎ እንደነበር አይረሳም። 

Advertisements