ጆሴ ሞውሪንሆ / የፖርቹጋላዊው አለቃ መግለጫ ውላቸውን በማራዘም፣ በሳንቼዝና ማኪቴሪያን፣ በሾው እና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ

ማንችስተር ዩናይትድ በሳምንቱ ከባድ መርሀ ግብር ወደተርፍ ሙር በማምራት በርንሌይ ይገጥማል። ከዛሬ አመሻሹ ፍልሚያ በፊትም ፖርቹጋላዊው የክለቡ አለቃ ጆሴ ሞውሪንሆ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ የሰጡበትን ጋዜጣዊ መግለጫ ሙሉ ቃል ይዘን ተገኝተናል።


በቫሌንሲያ ዙሪያ

“እሱ አምበላችን ነው። እሱን ዝምተኛው መሪ ብዬ እጠራዋለሁ። በሜዳ ላይ ግን ልምዱን እና የማሸነፍ ፍላጎቱን ያሳያል በግራ እግሩ የሚያስቆጥረው ግብም አስደናቂ ነው። … እሱ እጅግ ጥሩ ተጫዋች ነው።” 

በሉክ ሾው ዙሪያ

“እሱ ጥሩ ይጫወታል። ለረጅም ጊዜ ሳላጫውተው ቆይቼ የመሰለፍ እድል ስሰጠው ተሻሽሎና ጥሩ መጫወት ችሎ ታይቷል።

“ለመጀመሪያ ጊዜ በቻምፒየንስ ሊግ ግጥሚያ ያደረገውን ጨዋታ አስታውሳለሁ። ከኤቨርተን ጋር በነበረው ጨዋታ እንዳደረገው በሂደት መሻሻልና በጨዋታዎች ላይ በጥሩ መንገድ መጓዝ ችሏል። 

“… በአካል ብቃት የተሻለ፣ በአዕምሮ ደረጃ ጠንካራ፣ በታክቲክ ረገድ ጨዋታውን መረዳት የሚችል እንዲሁም ደግሞ በተለያየ ደረጃ ለምንፈልገው ብቃት ዝግጁ ሆኗል። 

“በሁኔታው በጣም ደስተኛና በዚህ ሰአት (በዝውውር ገበያው) ከሉክ ሾው የተሻሉ ብዙ የግራ መስመር ተከላካዮች አለማየቴን መናገር እችላለሁ።” 

በውል ማራዘሚያ ስምምነታቸው ዙሪያ

“የውል ስምምነቴ የሚያበቃው ሀምሌ 2019 ነው። ስለዚህ በውል ማራዘም ዙሪያ ንግግር ለማድረግ በጣም ብዙ ጊዜ አለ። ክለቡ እና ባለቤቶቹ እንዲሁም ቦርዱ በእኔ ደስተኛ እንደሆኑ አውቃለሁ። 

“እኔም በዩናይትድ ቆይታዬ ደስተኛ እንደሆንኩ ያውቃሉ። ነገሩ እንደዚህ ከሆነ ደግሞ አንድ ቀን ውሳኔ ስናሳልፍ በቀላሉ የውል ስምምነት እናደርጋለን። 

ማኪቴሪያን ከነገው ጨዋታ ውጪ በመደረጉ ዙሪያ 

“ማኪቴሪያን ከቅዳሜው (ከነገው) ጨዋታ ውጪ መሆኑ ተረጋግጧል። ነገርግን ከጨዋታ ውጪ የተደረገው ጉዳት ስላለበት አይደለም። 

” እሱ ለጨዋታው አልተመረጠም። ነገርግን በጥሩ ሁኔታ ላይ ሆኖ ልምምድ እየሰራ ሲሆን እንደሌሎቹ የቡድኑ አባላትም በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል።” 

በዝውውር ጉዳይ ላይ ስላላቸው ሚና 

“አንዳንድ ጊዜ ሰዎች የዝውውር ጉዳይ አሰልጣኞችን በትልቁ የሚያሳትፍ አድርገው ያስቡታል። እንደማስበው ይህ ነገር በየክለቦቹ ሁኔታና እኛ (አሰልጣኞች) ስራችንን በምናስኬድበት መንገድ ላይ የሚወሰን ነው። 

“እኔን በተመለከተ ከዝውውር ድርድሮች ላይ እራሴን አገላለሁ። ከዛም የድርድሩን ዜና ነው የምጠብቀው። ከዛ ውጪ ባለ ነገር ውስጥ ጣልቃ አልገባም።

“አንድ ቀን እሱን (ሳንቼዝን) ካስፈረምነው ከእናንተ ጋር እናወራለን። ስለእሱ እና ለቡድናችን ሊያመጣልን ስለሚችለው ነገር እናወራለን። 

“እሱ የአርሰናል ተጫዋች ነው። እሱ የእኔ ተጫዋች አይደለም። ሊሳካም ላይሳካም ለሚችል ነገር የማወራበት ምክንያት የለኝም። 

“እኔ በሁኔታው ላይ ያለኝ ተሳትፎ ተጫዋቹን እወደዋለሁ ወይስ አልወደውም በሚለው ላይ ነው። ከዛ ውጪ ምንም የለኝም። ከጉዳዩ እራሴን አውጥቻለሁ።”

በሳንቼዝ ዝውውር ዙሪያ አዳዲስ ነገር

“እንደማስበው እኛ ወደዛ ስናመራና የአርሰናል አሰልጣኝ በግልፅ ስለጉዳዩ ሲያወሩ ሁሉም ነገሩን አውቆታል። ምንም የሚደበቅ ወይም የሚካድ ነገር የለም።

“ነገርግን ምንም የተጠናቀቀ ነገር የለም። ስለዚህም ማኪቴሪያን የእኛ ተጫዋች ነው። ሳንቼዝ ደግሞ የአርሰናል ተጫዋች ነው። ስለዚህም እኔ ፍላጎቴ በነገው ወሳኝ ነገር ላይ ማለትም በጨዋታው ላይ ትኩረት ማድረግ ነው።” 

Advertisements