ማይክል ካሪክ በውድድር አመቱ መጨረሻ ጫማውን ይሰቅላል፡፡በዩናይትድ የአሰልጣኞች አባል ውሰጥም ይካተታል፡፡

3.jpg

ዩናይትዶች “ያልተዘመረለት ጀግና” እያሉ የሚያሞካሹት ከአስር አመታት በላይ የቀያይ ሰይጣኖቹ በአማካይ ቦታን ሲመራ የቆየው አማካዩ ማይክል ካሪክ በውድድር አመቱ መጨረሻ ጀምሮ ጫማውን የሚሰቅል ሲሆን በአዲስ ምእራፍ የቡድኑ የመጀመሪያው ቡድን የአሰልጣኞች አባል ሆኖም እንደሚቀጥል ጆሴ ሞሪንሆ አሳውቀዋል፡፡


<!–more–>


እየተካሄደ ባለው የ 2017/2018 የእንግሊዝ ፕሪምየርሊግ በህመም እና በጉዳት በሜዳ ላይ ቡድኑን ማገልገል ያልቻለው ቀድሞ የቶተንሀም ሆትስፐር አማካይ ማይክል ካሪክ ከውድድር አመቱ መጨረሻ ጀምሮ ጫማውን ይሰቅላል፡፡

አማካዩ ከቀያይ ሰይጣኖቹ ጋር ለተጨማሪ አንድ አመት ኮንትራቱን ባለፈው ክረምት ላይ ካራዘመ በኋላ ባጋጠመው ህመም መለስተኛ የልብ ቀዶ ጥገና እስከ ማድረግ ደርሶ የነበረ በመሆኑ ቡድኑና ማገልገል ሳይችል ቆይቷል፡፡

5.jpg

ከህመሙ አገግሞ ወደ ልምምድ የተመለሰው ካሪክ እስከ ውድድሩ አመቱ መጨረሻ ድረስ ለቀያይ ሰይጣኖቹ ጋር ኮንትራት ያለው ሲሆን ሲሆን ከቀጣዩ አመት በኋላ ግን ጫማውን ሰቅሎ በአዲስ ምእራፍ ወደ አሰልጣኞች አባላት የሚቀላቀል ይሆናል፡፡

በቀጣዩ ነሀሴ ወር ላይ እድሜው 37 የሚሞላው አማካይ  ከማንቸስተር ዩናይትድ አለቃ ጆሴ ሞሪንሆ ከቀጣይ አመት ጀምሮ የቡድኑ አሰልጣኞች አባል እንዲቀላቀል የቀረበለትን ጥሪ በአዎንታ ተቀብሎታል፡፡ካሪክ ቀሪዎቹን የውድድር አመታት የመጫወት እድሉ ጠባብ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን ከአሁን በኋላ የቡድኑን ማሊያ ሳይለብስ ቀጣይ ስራው የመጀመር እድሉ የሰፋ ሆኗል፡፡

“ለቡድኑም ይሁን ለሱ ያለ ጉዳት ወይንም ያለምንም ችግር የእግርኳስ ህይወቱን ማጠናቀቁ ጥሩ ውሳኔ ነው፡፡በዚህ ሁላችንም ደስተኞች ነን፡፡ስለዚህ በአመቱ መጨረሻ ሀሳቡን ካልቀየረ በቀር የቡድናችን አሰልጣኞች አባል ይሆናል፡፡ክለቡም ይህን በማድረጉ በጣም ደስተኛ ነው፡፡ እኔም እንዲሁ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡” ሲሉ ጆሴ ተናግረዋል፡፡

ጆሴ ተጫዋቹ ለጥቂት ወራት ከልምምድ ውጪም ቢሆን ለቡድኑ አስፈላጊ ተጫዋች እንደነበረ በመናገር ተጫዋቹ ከሜዳ ውጪም ምን ያህል ሲጠቅማቸው እንደነበር ጨምረው ተናግረዋል፡፡

6.jpg

ካሪክ 2006 ላይ ወደ ዩናይትድ ከተቀላቀለ በኋላ ለክለቡ በ 459 ጨዋታዎች ላይ ለዋናው ቡድኑ መጫወት የቻለ ሲሆን በቆይታው አምስት ፕሪምየርሊግ ዋንጫዎችን መሳም ችሏል፡፡2008 ላይ ባለ ትልቁን የአውሮፓ ቻምፕየንስ ሊግን ካነሳው የቡድኑ ስብስብ ውስጥም እንደነበር ይታወሳል፡፡

የአለም ክለቦች ዋንጫ፣የኤፍ ኤ ካፕ እና የዬሮፓ ሊግን አንድ አንድ ጊዜ ሲያነሳ የሊግ ካፕን ደግሞ ሶስት ጊዜ አሸንፏል፡፡የእንግሊዝ አሸናፊዎች አሸናፊ የሚባለው የኮሚውኒቲ ሺልድን ደግሞ ስድስት ጊዜ በማሸነፍ ከቀያይ ሰይጣኖቹ ጋር የማይረሳ ጊዜን አሳልፏል፡፡

ተጫዋቹ በክለቡ ደጋፊዎች ብቻ ሳይሆን በሌሎች ክለቦች ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች አድናቆት ከሚሰጣቸው ጥቂት እንግሊዛውያን ውስጥ ይካተታል፡፡ከዚህ ቀደም ስለ እሱ ከተሰጡት አስተያቶች ውስጥ፡-

“ካሪክ ለባርሴሎናም መጫወት ይችላል፣ጥሩ እይታ ያለው እና ምርጥ ተጫዋችም ነው፡፡” – አርሴን ዌንገር

“በአንጻራዊነት እስካሁን ካየኋቸው ምርጡ የተከላካይ አማካዮች ውስጥ አንዱ ካሪክ ነው፡፡”- ፔፕ ጓርዲዮላ

“ስኮልስ እና ካሪክ በአንድ ላይ ሲጫወቱ የአማካይ ቦታው ሰላም ያገኛል፡፡ልክ ወደ ባር አቅንተህ ፒያኖን እየሰማህ እንደ መዝናናት ነው፡፡” –  ጋሪ ኔቭል

“ካሪክ ዩናይትዶች ሚዛናዊ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፣መከላከልም ይችላል፡፡ጥሩ አድርጎ ማቀበል እና ጥሩ ኳሶችን ወደ ጎል መምታት የሚችል የተሟላ ተጫዋች ነው፡፡” – ዣቪ ሄርናንዴዝ

ጆሴ በ 12 አመታት 18 ዋንጫዎችን ማሳካት የቻለው አማካያቸው ያሳለፈው ስኬታማ ቆይታ ለቀጣዩ ወጣት ተጫዋቾች እንዲያካፍልላቸው ፍላጎት አላቸው፡፡ታማኝ አገልጋይነቱ ለሌሎች ተጫዋቾች አርአያ እንዲሆን ይፈልጋሉ፡፡በዚህም ምክንያት አብሯቸው እንዲሰራ ያቀረቡት ጥያቄ ተጫዋቹ ስምምነቱን ገልጾላቸዋል፡፡

Advertisements