በታላቁ የለንደን ማራቶን ቀነኒሳ በቀለ ፣ ሞ ፋራህ እና ኢሉድ ኬፕቾጌ ይፋጠጣሉ


ሶስቱ ታላላቅ የረጅም ርቀት አትሌቶች ቀነኒሳ በቀለ ፣ ሞ ፋራህና ኢሉድ ኪፕቾጌ በቀጣዩ ሚያዚያ ወር የሚካሄደውን የቨርጅን መኒ ለንደን ማራቶን እንደሚሳተፉ የውድድሩ አዘጋጆች አሳውቀዋል፡፡

የዓለማችን የ10,000 ሜትርና የ 5000 ሜትር ባለክብረወሰኑና የማራቶን ሁለተኛ ፈጣን ሰዓት ባለቤቱ ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ መወሰኑን ያሳወቁት የውድድሩ አዘጋጆች የሶስቱ አትሌቶች መፋጠጥ ታላቁን ማራቶን ድምቀት እንደሚያላብሰው ተናግረዋል፡፡

ቀነኒሳ ያለፉትን ሁለት የለንደን ማራቶኖች የተሳተፈ ሲሆን በ2016 ሶስተኛ ሆኖ ሲጨርስ የአምናውን ውድድር ደግሞ በኬንያዊው ዳንኤል ዋንጂሩ ተቀድሞ በሁለተኝነት ማጠናቀቅ ችሏል፡፡
ቀነኒሳ በውድድሩ መሳተፉን አስመልክቶ በሰጠው አስተያየት “ለሶስተኛ ተከታታይ ጊዜ በዚህ ውድድር መካፈል በመቻሌ ደስተኛ ነኝ፡፡ ካለፈው አመት አንድ ደረጃ ከፍ ያለ ውጤት ለማስመዝገብ እጥራለሁ ፤ ይህም ውድድሩን በአንደኝነት መጨረስ ነው”

“ከዓለማችን ታላላቅ የረጅም ርቀት ሯጮቹ ሰር ሞ ፋራህ፣ ኪፕቾጌና ሌሎች ጋር ለማደርገው ፉክክር እየተዘጋጀሁ ነው፡፡ እስከሚያዚያ ድረስም ወደምርጥ አቋሜ ለመመለስ እተጋለሁ ” ብሏል፡፡

የውድድሩ ዳይሬክተር ሁዝ ብራሸር በበኩላቸው “ይህ እጅግ አጓጊ ፍልሚያ ነው፡፡ ለምንጊዜውም የርጅም ርቀት ንጉስነት የሚደረግ ፉክክር ሲሆን ሶስቱ አትሌቶችም ለመጀመሪያ ጊዜ በማራቶን መድረክ የሚገናኙበት ይሆናል ” ሲሉ ገልፀዋል፡፡

Advertisements