ኬቨን ዴብሩይን በማንችስተር ሲቲ ያለውን ውል አራዘመ

በውድድር አመቱ እጅግ ድንቅ አቋም ማሳየቱን የተያያዘውና ለማንችስተር ሲቲ አስደናቂ ግስጋሴ ትልቁን ድርሻ በመወጣት ላይ የሚገኘው ቤልጅየማዊ በውሃ ሰማያዊዎቹ ቤት ለተጨማሪ አመታት የሚያቆየውን ውል ፈርሟል፡፡

ለአራት ዋንጫዎች እየተወዳደረ የሚገኘው ማንችስተር ሲቲ በዚህ ሳምንት የተጫዋቾቹን ውል ማራዘሙ ላይ በትጋት እየሰራ የሚገኝ ሲሆን ቤልጅየማዊው አማካይም ከኒኮላስ ኦታመንዲና እና ፈርናንዲንሆ በመቀጠል ሶስተኛው ፈራሚ ሆኗል፡፡

ኮከቡ በሳምንት 280,000 ዩሮ የሚያስገኝለትን ውል የፈረመ ሲሆን በሂደትም ሳምንታዊ ደመወዙ እስከ 350,000 ዩሮ ሊደርስ እንደሚችል በስምምነቱ ላይ ሰፍሯል፡፡

የጨዋታ አቀጣጣዩ ከፊርማ ስነስርአቱ በኋላ በሰጠው አስተያየት ” ሲቲ እንደቤቴ የማየው ክለብ ነውና በዚህ ለመቆየት አላንገራገርኩም፡፡ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ድንቅ እግር ኳስን ለአለም እያበረከትን ነው፡፡  የዚህ አካል መሆን የሚያኮራ ሲሆን በቀጣይ አመታት የምንደርስበት የስኬት ደረጃ ያጓጓኛል” ብሏል፡፡

እስከ 2023 ድረስ በኢትሃድ ለመቆየት የተስማማው ኬቨን በ2015 ከጀርመኑ ዎልፍስበርግ ማንችስተር ሲቲን ከተቀላቀለ በኋላ 122 ጨዋታዎችን አድርጎ 31 ጎሎችን ማስቆጠር ሲችል 50 ጎል የሆኑ ኳሶችን አቀብሏል፡፡

Advertisements