የተረጋገጠ/ሄነሪክ ሚኪታሪያን ለአርሰናል ፈረመ

በማንችስተር ዩናይትድ እምብዛም ስኬታማ ያልሆነ አንድ አመት ተኩልን ያሳለፈው አርሜኒያዊ ኮከብ ሄነሪክ ሚኪተሪያን ለሰሜን ለንደኑ አርሰናል በይፋ ፊርማውን አኑሯል፡፡

በጆዜ ሞሪንሆ አማካኝነት ከጀርመኑ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ማንችስተር ዩናይትድን በ 2016 የተቀላቀለው ጥበበኛ አማካይ ዝውውሩን ያደረገው በሁለቱ ክለቦች መካከል በተደረገ ቀጥተኛ የተጫዋቾች ቅይይር ሲሆን በተቃራኒውም አሌክሲስ ሳንቼዝ ማንችስተር ዩናይትድን ተቀላቅሏል፡፡

ለቀናት የአለምን የስፖርት ሚዲያ ተቆጣጥሮት የቆየው የሁለቱ ተጫዋቾች ዝውውር ጉዳይ ዛሬ ማምሻውን እልባት አግኝቶ ተጫዋቾቹ ፊርማቸውን በይፋዊ ስነስርአት አኑረዋል፡፡

ከፊርማ ስነስርአቱ በኋላ አስተያየቱን ለአርሰናል ድረ ገፅ የሰጠው ሚኪታሪያን “ድርድሩ በስኬት በመጠናቀቁ ደስተኛ ነኝ ፤ ለረጅም ጊዜ የመጫወት ህልሜ ለነበረው ለአርሰናል በመፈረሜ ወደር የለሽ ደስታ ተሰምቶኛል ” ብሏል፡፡
የአርሰናል አሰልጣኝ አርሰን ዌንገር በበኩላቸው “ሚኪ እጅጉን የተሟላ ተጫዋች ነው ፤ ዕድሎችን መፍጠር ይችላል፡፡ በከላከሉም ላይ ጥሩ ነው፡፡ቦታዎችን በሚገባ የመሸፈን አቅም አለው፡፡ ሚኪ ለቡድኔ ሁሉንም አይነት ግልጋሎት መስጠት የሚችል ተጫዋች ነው” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

የቀያይ ሰይጣኖቹ አለቃ ጆዜ ሞሪንሆ በበኩላቸው የአሌክሲስ ሳንቼዝ የፊርማ ስነስርአት ላይ በተጓዳኝ ስለሚኪታሪያን ባደረጉት ንግግር “ለሚኪ ስኬታማና ደስተኛ ቆይታን እመኝለታለሁ ፤ በርግጠኝነት ይሳካለታል፡፡ እዚህ ዩናይትድ ቤት ውስጥ በቀላሉ የሚረሳ ተጫዋች አይደለም፡፡ በተለይ በዩሮፓ ሊግ ላይ ላበረከተልን አስተዋፅኦ እናመሰግነዋለን፡፡” ብለዋል፡፡

Advertisements