የተረጋገጠ / ማንችስተር ዩናይትድ የአሌክሲስ ሳንቼዝን ዝውውር አጠናቀቀ

ማንችስተር ዩናይትድ ሄነሪክ ማኪቴሪያንን በልዋጭ የሰጠበትን የአሌክሲ ሳንቼዝ ዝውውር አጠናቋል። 

ካሳለፍነው ክረምት በፊት ጀምሮ ወደማንችስተር ሲቲ እንደሚያመራ እየተነገረ የቆየው ቺሊያዊው ኮከብ የኢትሀዱ ክለብ ለዝውውሩ በአርሰናል የተጠየቀውን ትልቅ ገንዘብ እና የተጫዋቹን ከፍተኛ ሳምንታዊ ደሞዝ ለመክፈል ባለመፈለጉ ቺሊያዊው ኮከብ በተቀናቃኙ ዩናይትድ በእጁ ሊገባ ችሏል።

ሳንቼዝ ነሀሴ 2012 ላይ ሮበን ቫንፐርሲ በ 23 ሚሊዮን ፓውንድ የዝውውር ሂሳብ ዩናይትድን ከተቀላቀለ በኋላ አርሰናልን ለቆ የኦልትራፎርዱን ክለብ የተቀላቀለ ሁለተኛው ትልቅ ተጫዋች ሆኗል። 

የቺሊያዊው ክለቡን መልቀቅም ለኢምሬትሱ ክለብ ጎጂ ተደርጎ ቢታይም የክለቡን የተረበሸ አየር ወደቀደመ ቦታው ለመመለስ እንደሚጠቅም የሚጠበቅ ሲሆን በልዋጭ መልክ አርሰናል እጁ የገባው አርሜኒያዊው ኮከብ ማኪቴሪያንም ካለው ተሰጥኦ አንፃር ለአርሰናል ጥሩ ግልጋሎት ሊሰጥ እንደሚችል ይታሰባል።

ሳንቼዝ ከዝውውሩ መጠናቀቅ በኋላም “የአለማችንን ትልቅ ክለብ ለመቀላቀል ጓጉቼ ነበር። በአርሰናል አስደናቂ የሶስት አመታት ከግማሽ ቆይታን አድርጌያለሁ። ከታላቁ ክለብም እና ከደጋፊዎቹም አዎንታዊ ትውስታን ይዤ መጥቻለሁ።

“በዚህ ታሪካዊ ስታዲየም እና ከጆሴ ሞውሪንሆ ጋር በጋራ የመስራት እድል እምቢ ማለት የምችለው አይነት አልነበረም። 

“ለዩናይትድ ዋና ቡድን መጫወት የቻልኩ የመጀመሪያው ቺሊያዊ በመሆኔ እኮራለሁ። በአለም ላይ ላሉ የቡድኑ ደጋፊዎችም ለምን ክለቡ እንዳመጣኝ ማስመስከር እንደምችል ተስፋ አደርጋለሁ።” በማለት በሁኔታው የተሰማውን ደስታ ለዩናይትድ ይፋዊ ድረገፅ ገልጿል።

የሳንቼዝ ዝውውር መጀመሪያ ከነበረበት ሂደት ባልታሰበ መልኩ የተጠናቀቀ ሲሆን ለረጅም ወራትም ሲያነታርክና እርስበርሳቸው የሚጋጩ ሁነቶችን ሲያስመለክት ቆይቶ በመጨረሻ መቋጨት ችሏል።

​ከትናንት በስቲያ እንኳን አንድ ፓውሊያ ሶቢዬርጄስካ የተሰኘች ተማሪ ቺሊያዊው አጥቂ ባሳለፍነው አመት መጠጥ ቤት ውስጥ አግኝቷት ካወራት በኋላ አብረወወ ወሲብ እንዲፈፅሙ 1,000 ፓውንድ እንደሰጣት መግለጿን ተከትሎ ሳንቼዝ ጉዳዩን ለማስተባበል ተገዷል።

ከዚህ ቀደም ወደሲቲ ለማድረግ ያሰበው ዝውውሩ እየተንጓተተ ባስቸገረውና እንደፈለገው አልጓዝ ባለው ሰአትም በጨዋታ ላይ ተቀይሮ ከሜዳ እንዲወጣ በሚደረግ ሰአት ያልተገባ ባህሪን በማሳየት ደጋፊውን ሲያስቆጣ መታየቱ አይረሳም። 

ሳንቼዝ ባሳለፍነው ክረምት ወደሲቲ ሊያደርገው የነበረው ዝውውር እውን ሊሆን ተቀርቦ በመጨረሻ ሳይሳካ የቀረውም በቬንገር ግትር አቋም እንደነበር ይታወሳል። 

Advertisements