ሽኝት/ ባርሴሎና ሀቭየር ማሼራኖ ከክለቡ መልቀቁን ይፋ አደረገ

ከሊቨርፑል 2010 ላይ ከተዘዋወረ በኋላ ከካታላኑ ክለብ ጋር 18 ዋንጫዎችን ማንሳት የቻለው ማሼራኖ ከሰባት አመት ከግማሽ በኋላ ከባርሴሎና ጋር መለያየቱ እርግጥ ሆኗል፡፡

ማሼራኖ በባርሴሎና የመሀል ተከላካይ በመሆን ባለፉት  አመታት ውጤታማ ቆይታ ቢኖረውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በቋሚነት ቡድኑን ለማገልገል አልቻለም፡፡

በተለይ ባርሴሎና ሳሙኤል ኡምቲቲን ካዘዋወረ በኋላ በቦታው ላይ ጠንካራ ፉክክር የገጠመው ሲሆን ከእድሜ መግፋት ጋር ቦታውን መልሶ ለማግኘት አልቻለም፡፡

ማሼራኖ ከባርሴሎና ጋር ለመለያየት ያቀረበው ጥያቄ ክለቡ የተጫዋቹን ፍላጎት በመረዳት እንደለቀቀው አሳውቋል፡፡ ሰባት አመት ከግማሽ ያገለገለውን ተጫዋችም ነገ እሮብ ባዘጋጀው ፕሮግራም ላይ በክብር እንደሚሸኘው ነው ያሳወቀው፡፡በሮግራሙ ላይም የክለቡ ፕሬዝዳንት ጆሴ ማሪዮ ባርቶሚዮ ጨምሮ የዋና ቡድን ተጫዋቾች የሚገኙ ይሆናል

ተጫዋቹ ከባርሴሎና ጋር በ 334 ጨዋታዎች ላይ መሰለፍ የቻለ ሲሆን በቆይታው በአምስት አሰልጣኞች የመሰልጠን እድል አግኝቷል፡፡በክለቡም ከሊዮ ሜሲ፣ፍሊፕ ኮኩ እና ዳኒ አልቬዝ በመቀጠልም ብዙ ጨዋታዎችን መጫወት የቻለ ተጫዋች መሆን ችሏል፡፡

በተለይም የተከላካይ አማካይ ሚናን በመተው የተጎዱ ተጫዋቾች ቦታን በተከላካይነት በመሸፈን ያደረገው አስተዋጽኦ በክለቡ ደጋፊዎች ጭምር እንዲወደድ አድርጎታል፡፡

ማሼራኖ ደሞዙን በሶስት እጥፍ ለማሳደግ ፍላጎት ላሳየው ለቻይናው ሱፐርሊግ ለሚሳተፈው ለሂቤይ ፎርቹን እንደሚፈርም የሚጠበቅ ሲሆን በአዲሱ ክለቡም የሀገሩን ልጅ ኤዝክዌል ላቬሲን የሚያገኝ ይሆናል፡፡

Advertisements