የተረጋገጠ/ላዛና ዲያራ ፓሪስ ሴንት ጀርሜይንን ተቀላቀለ

የቀድሞው የአርሰናል፣ የቼልሲና የሪያል ማድሪድ አንጋፋ አማካይ ላሳና ዲያራ አልጀዚራን ለቆ ወደአገሩ በመመለስ ለቱጃሩ ፓሪስ ሴንት ጀርሜይን ለመጫወት ፊርማውን አኑሯል፡፡

የ32 አመቱ የተከላካይ አማካይ በአልጀዚራ የነበረው ውል መጠናቀቁን ተከትሎ ከተለያዩ ክለቦች ጋር ሲያያዝ ቢቆይም የፈረንሳዩን መዲና ክለብ መዳረሻው ያደረገ ሲሆን በክለቡም ለ18 ወራት የሚያቆየውን ውል ፈርሟል፡፡

በ2016ቱ የፈረንሳይ የአውሮፓ ዋንጫ ዶሮዎቹን ወክሎ መጫወት የቻለው ዲያራ ከፊርማ ስርአቱ መጠናቀቅ በኋላ ለክለቡ ድረ ገፅ በሰጠው አስተያየት “ወደአደግኩበት ከተማ ክለብ በመምጣቴ ደስተኛ ሆኛለሁ፡፡ ፔዤ ብዙ ነገሬን ይወክላል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያደገ የመጣውን የክለቡን አለም አቀፋዊ አቅም ተከትሎ ለፓሪሱ ክለብ መጫወት የብዙ ታላላቅ ተጫዋቾች ህልም ነው፡፡ ይህን ህልም እውን ማድረግ መቻሌ በራሱ እድለኝነት ነው፡፡ለክለቡ ያለኝን ሁሉ ለመስጠትና እኔን ወደዚህ ያመጡበት ውሳኔ ትክክል መሆኑን ማሳየት እፈልጋለሁ፡፡” ብሏል፡፡

የክለቡ ስራ አስፈፃሚ ናስር አል ከላፊ በበኩላቸው “እንደላሳና አይነት ጥራት ያለው ተጫዋች ማግኘት በመቻላችን ደስተኞች ነን ፤ በሌሎች አገር ሊጎችም ሆነ በፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ሰፊ ልምድን አካብቷል፡፡ ለአሰልጣኞች ቡድናችን ጥሩ አማራጭን ይፈጥራል፡፡ የፓሪስ ነዋሪ እንደመሆኑም ከክለባችን ደጋፊዎች ሞቅ ያለ አቀባበል ይጠብቀዋል ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ላሳና ዲያራ የትልቅ ደረጃ እግር ኳስ ህይወቱን በፈረንሳይ ሊግ 1 ለ ሃርቬ በመጫወት የጀመረ ሲሆን ወደእንግሊዝ በመሻገርም በቼልሲ ፣ በአርሰናልና ፖርትስማውዝ ቆይታ አድርጓል ፤ ቀጥሎም ወደስፔን አቅንቶ ለሪያል ማድሪድ የተጫወተ ሲሆን ከሶስት አመታት የስፔን ቆይታው በኋላ ወደሩሲያ በማቅናት ለአንዚ ማካቻካላና ሎኮሞቲቭ ሞስኮ መጫወት ችሏል፡፡

በ2015 ወደአገሩ በመመለስ ለሁለት አመታት ለኦሎምፒክ ማርሴይ የተጫወተው ጠንካራ አማካይ 2017 ፈረንሳይን ለቆ ወደመካከለኛው ምስራቅ በማቅናት ለአልጀዚራ ግልጋሎቱን ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

Advertisements