ሹመት / ፊል ኔቭል የእንግሊዝ የሴት ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ተደርጎ ተሾመ

2.jpg

እንግሊዛዊው የቀድሞ የማንችስተር ዩናይትድ እና የኤቨርተን ተጫዋች የነበረው ፊል ኔቭል ባለፈው መስከረም ወር ላይ ከሀላፊነታቸው ተሰናበቱት ማርክ ሲምፕሰን ተክቶ የእንግሊዝ የሴት ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆኖ ተሹሟል፡፡1.6 ሚሊየን ተከታታይ የነበረው ይፋዊ  የትዊተር አካውንቱን ግን ለምን ፈጥኖ ሊያጠፋው ቻለ?

የእንግሊዝ እግርኳስ ፌዴሬሽን እንዳሳወቀው ከሆነ ፊል ኔቭል እስከ 2021 የሴቶች የአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ ድረስ ብሄራዊ ቡድኑን እያሰለጠነ የሚቆይ መሆኑ አሳውቋል፡፡

የ 41 አመቱ የቀድሞ ተጫዋች በአለም ከጀርመን እና ከአሜሪካ በመቀጠል በሶስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠውን የእንግሊዝ የሴት ብሄራዊ ቡድን በመረከቡ መደሰቱን ተናግሯል፡፡

“የእንግሊዝ የሴት ብሄራዊ ቡድን እንዳሰለጥን በመመረጤ ኩራት ተሰምቶኛል፡፡”በማለት ቡድኑንም ወደ ቀጣ ምእራፍ አንድ ደረጃ ከፍ ለማድረግ እቅድ እንዳለው አሳውቋል፡፡

የሴቶች እግርኳስ ፌዴሬሽን ዳይሬክተር የሆኑት ባሮንስ ሱ ካምቤል በበኩላቸው “ፊል ኔቭልን በማግኘታችን ደስተኞች ነን፡፡በሱ ዙሪያም ትልቅ ቡድን እንገነባለን፡፡”ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

የሴት ቡድንን ማሰልጠን ልምድ የሌለው ፊል ኔቭል በእንግሊዝ ከ21 አመት በታች እንዲሁም ወደ ስፔን አቅንቶ የቫሌንሺያን የወንዶች ቡድን ማሰልጠን እንደቻለ ይታወቃል፡፡

ኔቭል ከዚህ ቀደም በትዊተር አካውንቱ በሴቶች መብት ላይ የተያያዙ ያልተገቡ መልእክቶችን በመለጠፍ ታወቅ የነበረ ሲሆን አሁን ግን የእንግሊዝ ሴት ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ተደርጎ ከተሾመ በኋላ 1.6 ሚሊየን ተከታታይ ያለውን የትዊተር አካውንቱን ማጥፋቱ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

በአንድ ወቅት “እንደምን አደራችሁ ወንዶች? ……”በማለት በትዊተር ገጹ ላይ የለጠፈው መልእክት ምነው ሴቶችን ረሳሀቸው? የሚል ጥያቄ ሲያስነሳ የመለሰው ምላሽ “ወንዶች እንዴት አደራችሁ ስል ሴቶች ቁርስ በማዘጋጀት ፣ልጆች ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ በማዘጋጀት እንዲሁም አልጋ ስለሚያነጥፉ…በጣም ስራ እንደሚበዛባቸው አስቤ ነው ….ኦው! ይቅርታ እንደምን አደራችሁ ሴቶች!”  በማለት አሽሟጦ ምላሽ የሰጠበት መንገድ ስለ ሴቶች ያልተገባ ነገር ከተናገራቸው ውስጥ የሚጠቀስ ነው፡፡

 

Advertisements