የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ማህበር 18 ሩሲያውያን አገራቸውን ሳይወክሉ እንዲወዳደሩ ፈቀደ

​ዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ማህበር ምንም እንኳን በመንግስት ደረጃ የሚደገፈውን የሩሲያ አትሌቶች አበረታች መድሃኒት ተጠቃሚነት ተከትሎ አገሪቷን ከሁሉም ውድድሮች ቢያግድም ንፅህናቸውን በምርመራ ያረጋገጡ 18 አትሌቶች አገራቸውን ሳይወክሉ በገለልተኝነት እንዲሳተፉ ፈቅዷል፡፡

የማህበሩ የአበረታች መድሃኒት ምርመራ ቦርድ ከ18 አትሌቶች የቀረበለትን ጥያቄ ተቀብሎ ምርመራውን ሲያደርግ ከሰነበተ በኋላ የአትሌቶቹን ንፅህና በማረጋገጡ በእገዳ ላይ ያለችውን አገር ሳይወክሉ በ2018 በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ እንዲሳተፉ አፅድቆላቸዋል፡፡
 ጥያቄው ከፀደቀላቸው አትሌቶች መካከል የአጭር ርቀት ተወዳዳሪዎች ፣ የርዝመትና የስሉስ ዝላይ ተወዳዳሪዎች ፣ የመዶሻና የጦር ውርወራ ተወዳዳሪዎች የሚገኙበት ሲሆን ጥያቄ ካቀረቡ በርካታ አትሌቶች መካከል ንፅህናቸው ተመርምሮ የተለዩ መሆናቸውን ማህበሩ ገልጿል፡፡

የማህበሩ ፕሬዝዳንት ሴባስቲያን ኮ በጉዳዩ ላይ በሰጡት መግለጫ “በሂደቱ ንፁህ አትሌቶችን ለመለየትና ለመደገፍ የቻልነውን ሁሉ አድርገናል ፤ ካለፈው አመት ጀምሮ የአትሌቶቹን ጉዳይ ስንመረምር የቆየን ሲሆን ምርመራው የተወሳሰበ እና ቀላል ባለመሆኑ ጊዜ ወስዶብናል፡፡ የምርመራውን ቦርድ ላደረገው ጥረትና ድጋፍ ለመሰግነው እወዳለሁ ” ብለዋል፡፡

Advertisements