አርሴን ዌንገር በሳንቲ ካዞርላ የኮንትራት ማራዘሚያ ዙሪያ አስተያየት ሰጡ

አርሴን ዌንገር በውድድር አመቱ መጨረሻ ላይ ኮንትራቱ የሚጠናቀቀው እና በጉዳት ከሜዳ ከራቀ ከአመት በላይ ያስቆጠረው የአማካይ ተጫዋቹ ሳንቲ ካዞርላ አዲስ የኮንትራት ማራዘሚያ ዙሪያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የአርሰናል የመሀል ሜዳ አቀጣጣይ የነበረው ሳንቲ ካዞርላ እግሩ ላይ ባጋጠመው ጉዳት ከሜዳ ከራቀ ከአመት በላይ አስቆጥሯል።

33ኛ አመቱ ላይ የሚገኘው ተጫዋች ከጥቅምት 2016 በኋላ ወደ ሜዳ ያልተመለሰ ሲሆን ጉዳቱ እስከ መጨረሻው ከጨዋታ ውጪ ሊያደርገው ተቃርቦ እንደነበር ሲነገር ቆይቷል።

በተደጋጋሚ ጊዜ እግሩ ላይ ያደረገው ቀዶ ጥገና እንዲሁን እድሜው እየገፋ በመምጣቱ እንደ ቀድሞው በምርጥ ብቃቱ ላይ ለመገኘት እንቅፋት እንደሚሆንበት ቢገመትም ተጫዋቹ ግን በ 2019 ላይ ወደ ምርጥ አቋሙ ለመመለስ እቅድ ይዟል።

ነገርግን አሁን ያለው ኮንትራቱ በውድድር አመቱ መጨረሻ ላይ የሚጠናቀቅ በመሆኑ በቀጣይነት ከአርሰናል ጋር ስለመቆየቱ ነገር የታወቀ ነገር የለም።

አርሰናል እንደ ዲያቢ እና ሮዝስኪ አይነት ጉዳት ያለባቸው ተጫዋቾችን በትእግስት ከጉዳታቸው እስኪመለሱ ድረስ በመጠበቅ የነበረውን ልምድ በካርዞላ ላይም ኮንትራቱን አድሶ ተጨማሪ እድል ይሰጠው እንደሆን የተጠየቁት ዌንገር ሲናገሩ

“እስከ አመቱ መጨረሻ ድረስ ለውጡን እንመለከተዋለን።ተጫዋቹ በአካል ብቃቱ ላይ ብቁ ከሆነ እና መጫወት የሚችል ከሆነ ኮንትራቱን እናራዝማለን። 

“ለዛም ነው ጉዳዩ የተወሳሰበ ነገር እንደሆነ የምነግራችሁ።ምክንያቱም በመጀመሪያ እሱን እንወደዋለን፣ሁለተኛ ደግሞ ትልቅ ተጫዋች ነው፣ነገርግን ሶስተኛው ነገር ፕሪምየርሊጉ የሚፈልገውን በፍጥነት ደረጃ ለመጫወት ዛሬ ላይ ጤነኛ መሆን አለብህ ስለዚህ ይህንን ስለመቋቋሙ በመጀመሪያ እሱን ጤናውን መመልከት አለብን

“አሁን ስለሱ የህክምና ሁኔታ በቂ መረጃ የለኝም።ከሁለት ሳምንት በፊት መልእክት ልኬበት ጥሩ ነገር ተመኝቼለታለው፣ በቅርቡም እንደምመለከተው ተስፋ አደርጋለው።እስካሁን ድረስ አልተመለሰም ምክንያቱም እግሩ ላይ ቀዶ ጥገና አድርጓል።” ሲሉ አርሰን ዌንገር ተናግረዋል።

Advertisements