ዱባይ ማራቶን/ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች አንፀባራቂ ድል አስመዘገቡ

የስታንዳርድ ቻርተርድ የዱባይ ማራቶን ዛሬ ማለዳ ላይ ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች ክብረ ወሰኖችን በማሻሻል ጭምር ድል አስመዝግበዋል፡፡

በወንዶቹ ውድድር በማራቶን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ስድስቱ የመጀመሪያ አትሌቶች በ 2:04:00 እና በ 2:04:15 መካከል በመግባት ታሪክ ሰርተዋል ፤ በተጨማሪም በሁለቱም ፆታዎች ኢትዮጵያውያኑ በመሃላቸው አንድ አትሌት ብቻ በማስገባት ከ 1-13 ያለውን ደረጃ በመያዝ አጠናቀዋል፡፡

በወንዶቹ ዘርፍ የተወዳደረው ሞስነት ገረመው በስፍራውን ክብረ ወሰን በማሻሻል ጭምር 2:04:00 በሆነ ሰዓት አንደኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ልዑል ገ/ስላሴ እና ታምራት ቶላ ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነው ጨርሰዋል፡፡ አሰፋ መንግስቱ ፣ ሲሳይ ለማ ፣ ብርሃኑ ለገሰ ፣ ሰይፉ ቱራ ፣የኔው አላምረው ፣ መኳንንት አየነውና ብርሃኑ ተሾመ ከ 4 እስከ 10 ያለውን ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁ አትሌቶች ናቸው፡፡

በሴቶች መካከል በተደረገው ውድድር ሮዛ ደረጀ በተመሳሳይ ክብረወሰን በማሻሻል 2:19:17 በሆነ ሰአት ያሸነፈች ሲሆን ፈይሴ ታደሰና የብርጓል መለሰ ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነው ጨርሰዋል፡፡

እነሱን ተከትለው ወርቅነሽ ደገፋ ፣ሃፍታምነሽ ተስፋይ ፣ ገለቴ ቡርቃ ፣ደራ ዲዳ ፣ ደሲ ጂሳ ፣ሰንበሬ ተፈሪና ሙልዬ ደቀቦ ከአራት እስከ አስር ያለውን ደረጃ ይዘው ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡

Advertisements